ሰኔ ፲፮( አሥራ ስድስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በመላው ኢትዮጵያ ከተቀሰቀሰው ሕዝባዊ እንቢተኝነት በኋላ በሰላማዊ መንገድ ገዥውን ሕወሃት ኢህአዴግን ይታገሉ የነበሩ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት ላይ ያነጣጠረ የጅምላ እስራት ተጠናክሮ መቀጠሉ ይታወሳል።
ከማእከላዊና በተለያዩ የማሰቃያ እስር ቤቶች ውስጥ ለዓመታት ሰቆቃ ሲፈሰምባቸው ከነበሩ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች መካከል በሰባቱ ላይ የፍርድ ብያኔ ተሰጠ። የልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት በእነ መቶ አለቃ ጌታቸው ከተከሰሱት ውስጥ አቶ በላይነህ ሲሳይ 4 ዓመት ከ 6 ወር፣ አቶ አለባቸው ማሞ 4 ዓመት ከ 2 ወር፣ አቶ ቢሆነኝ አለነ 4 ዓመት ከ6 ወር፣ አቶ ፈረጀ ሙሉ 4 ዓመት ከ 2 ወር፣ አቶ አትርሳው አስቻለው 4 ዓመት ከ 6 ወር፣ አቶ አንጋው ተገኘ 4 ዓመት ከ6 ወር፣ አቶ አባይ ዘውዱ ላይ ደግሞ 4 ዓመት ከ2 ወር እስራት ተፈርዶባቸዋል።
ተከሳሾቹ የቀረበባቸው ክስ ከ6 ዓመት ከ7 ወር በላይ ሊያስቀጣቸው የሚችል ቢሆንም ተከሳሾቹ በእስር ላይ እያሉ ባሳዩት መልካም ምግባር፣ የቤተሰብ ሃላፊ መሆናቸው እንዲሁም ከዚህ በፊት በማንኛውም ዓይነት የወንጀል ምግባር ላይ አለመሰማራታቸውን ከግምት በማስገባት ብያኔው ሊቀልላቸው እንደቻለ ፍርድ ቤቱ አስታውቋል። ባለፈው ሳምንት በተመሳሳይ ክስ ከተከሰሱት ተከሳሾች መካከል ስድስቱ በነጻ መለቀቃቸው የሚታወስ ነው።
በሰሜን ጎንደር የሰማያዊ ፓርቲ ከፍተኛ አመራር የነበረው 15ኛ አቶ አግባው ሰጠኝ በቂሊንጦ እስር ቤት ለደረሰው የእሳት ቃጠሎ ተጠያቂ ናችሁ ተብለው ከተከሰሱት በመቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ የክስ መዝገብ በመከሰሱ ከቀረበበት የሽብር ክስ ነጻ ቢባልም ከእስር አይፈታም። ላለፉት ሁለት ዓመታት ታስሮ የተፈታውና ድጋሜ በኮማንድ ፖስቱ ታስሮ በእስር ላይ የሚገኘው የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ አመራር አባል የነበረው አቶ ዳንኤል ሺበሺ አቃቤ ሕግ ባቀረበው ይግባኝ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርቧል። አቶ ዳንኤል ሺበሺ በቀረበበት ክስ ላይ የመከላከያ ምስክሮቹን አሰምቷል።
አቶ ግርማ ሰይፉ እና አቶ የሺዋስ አሰፋ የአቶ ዳንኤል ሺበሺ የመከላከያ ምስክር ሆነው ቀርበዋል። የአረና ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አብርሃ ደስታ በተመሳሳይ አቃቤ ሕግ ባቀረበው ይግባኝ መሰረት ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ቀጠሮ የነበረው ቢሆንም በችሎቱ ላይ አልተገኘም። ፍርድ ቤቱ አቶ አብርሃ ደስታ ለምን እንዳልቀረበ ላቀረበው ጥያቄ አቃቤ ሕግ ”ተከሳሽ አብርሃ ደስታን ልናገኘው አልቻልንም’ የሚል ምላሽ ሰጥቷል።
በመጨረሻም የአቶ ዳንኤል ሺበሺ የመከላከያ ምስክሮች ያቀረቡትን መከላከያ ፍርድ ቤቱ ከሰማ በኋላ አቶ ዳንኤል ሺበሺ ከኢሳቲ የቴሌቭዥን ጣቢያ ጋር አድርጎታል የተባለውን ቃለ መጠይቅ ንግግር በሲዲ ተገልቦጦ እንዲቀርብ ሲል ትእዛዝ ሰጥቷል። በተጨማሪም አቶ አብርሃ ደስታ ታስሮ እንዲቀርብ ሲል በይኖ ለሐምሌ 11ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ የጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል።