ሰኔ 15 ፥ 2009
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የሚካሄዱ የከፍተኛ ሊግ ጨዋታዎች ከትግራይ ክለቦች ጋር በተያያዘ የፕሮግራም መመሳቀልና ቀውስ እንደገጠመው መረጃዎች አመለከቱ።
በፌዴሬሽኑ የከፍተኛው ሊግ ኮሚቴው የወልዋሎ እና የሽሬ እንደስላሴ ክለቦች በአማራ ክልል ለመጫወት የማይችሉበት የፀጥታ ችግር መኖሩ በመረጋገጡ አዲስ ፕሮግራም የሚወጣበትና ቦታ መቀየር የተገደዱበት ሁኔት ተፈጥሯል።
ስለዚህም የመቀሌ ክለቦች በሙሉ ጨዋታቸውን በአዲስ አበባ ብቻ እንዲያደርጉ የሚያስችል አዲስ ፕሮግራም ማውጣቱን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በዚህም መሰረት ከሰኔ 21 እስከ ሰኔ 29/ 2009 ድረስ በወጣው አዲስ ድልድል መሰረት 3ስቱ የትግራይ ክለቦች ማለትም መቀሌ ከነማ፣ ሽሬ እንደስላሴ ወልዋሎ ከተጋጣሚዎቻቸው ጋር በአዲስ አበባ ከተማ እንዲጫወቱ ተወስኗል።
መቀሌ ከነማና ወልዋሎ ክለቦች ሲጫወቱ ብቻ ውድድሩ በመቀሌ እንዲካሄድ ሲወሰን ሌሎች ጨዋታዎችን ከተጋጣሚዎቻቸው ጋር ሲያደርጉ ግን በአዲስ አበባ ብቻ እንደሚጫወቱ ተገደዋል።
በትግራይ ክልል ርዕሰ ከተማ የመቀሌ ከነማ ከባህርዳር አቻው ጋር ከዚህ ቀደም ሲጫወት ደጋፊዎቹ ተጨዋቾችን በመደብደባቸው ጨዋታው መቋረጡና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽንም የተዛባ ነው የተባለ ውሳኔ መስጠቱ ይታወሳል።
በፌደሬሽኑ ውሳኔ የተበሳጩት የባህር ዳር ከነማ ደጋፊዎች እንዲሁም የአማራ ክልል ነዋሪዎች የትግራይ ክለቦች ወደ አከባቢያቸው መጥተው እንደሚጫወቱ ቢጠብቁም በጸጥታ ስጋት ምክንያት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሮግራሞቹን መሰረዙን መዘገባችን አይዘነጋም።
በፌደሬሽኑ ጨዋታዎች መሰረዝ ምክንያት ያደረገው የአማራ ክልል የተለያዩ ቢሮዎች የጸጥታ ችግር መኖሩን በማረጋገጣቸውና ዋስትና አላገኘሁም በሚል እንደሆነ ለክለቦቹ በጻፈው ደብዳቤ ገልጿል።
ይህንን ተከትሎም አዲስ ፕሮግራም በማውጣት የትግራይ ክለቦች አዲስ አበባ ላይ ከተጋጣሚዎቻቸው ጋር እንዲጫወቱ አዲስ ፕሮግራም አውጥቷል።
አሁን ባለው መረጃ ደግሞ በአማራ ክልል ያሉ ክለቦች አዲስ አበባ ሄደው ለመጫወት ፍላጎት እንደሌላቸው በመግለጽ ላይ መሆናቸውን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።