ሰኔ 14 ፥ 2009
በእርስ በርስ ጦርነት የምትታመሰውን ደቡብ ሱዳንን ለቀው ወደ ጋምቤላ የተሰደዱ ስደተኞች በክልሉ ደህንነትና ፀጥታ ላይ ውጥረት መፍጠራቸው ተገለፀ።
ሰኔ 13/ 2009 ዓ/ም የሚከበረውን የአለም የስደተኞች ቀን ባለፉት አመታት በእርስ በርስ ጦርነት የምትታመሰውን ደቡብ ሱዳን እየሸሹ ለሚሰደዱ ደቡብ ሱዳናውያን ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ የአለም አቀፍ የህክምናና ሰብዓዊ እርዳታ የሚሰጠው የድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድን (RSF) አስታውቋል።
ድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድን ከ1.8 ሚሊዮን በላይ የሆኑ ደቡብ ሱዳናዊያን የእርስ በእርስ ጦርነቱን በመሸሽ በአካባቢው በሚገኙ የጎረቤት ሀገሮች ለመሰደድ የተገደዱ ሲሆን ፥ ከእነዚህ ቁጥር ውስጥ ከ 378 ሺህ በላይ የሚሆኑት በኢትዮጵያ ጋምቤላ ክልል እንደሚገኙ አስታውቋል። ቡድኑ አያይዞ እንደገለፀው በአሁኑ ወቅት የደቡብ ሱዳን የፀጥታ ሁኔታ ተስፋ አስቆራጭ እየሆን በመምጣቱ ጦርነቱን እየሸሹ ወደ ጋምቤላ የሚገቡት ደቡብ ሱዳናውያን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጨምር አስታውቀዋል።
ድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድን ገለፃ እንደሚያሳየው አብዛቦዎቹ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ጋምቤላ ሲደርሱ በረሃብና በሽታ የተጠቁ ፣ የመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሽን ህመሞች ያጋጠማቸው በመሆኑ በክልሉ ወረርሽኝ ሊያስከትል እንደሚችል ስጋታቸውን ገልፀዋል። የጤና መታውኩ በሂደት ወደ አለመረጋጋትና የፀጥታ ችግር ሊያመራ እንደሚችልና በአካባቢው የታጣቂዎች መበራከት ክልሉን ወደ ቀውስ ሊመራው እንደሚችል አስታውቋል።