ሰኔ ፲፬( አሥራ አራት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአማራ ክልል ፓሊስ ኮሚሽን በመረጃ ሠራተኝነት ስትሰራ የነበረችው እና “ቦታ አሰጣችኋለሁ” በማለት ከባህር ዳር ነጋዴወችና ከተለያዩ
ግለሰቦች ከ470.00ሺህ ብር በላይ ገንዘብ በመቀበል ክስ ተምስርቶባት ታስራ የነበረች ሴት በትዕዛዝ ተፈትታ አሁንም በደህንነትና ስለላ ሥራ መሰማራቷ ተጠቆመ።
በፈጸመችው የማጭበርበር ወንጀል ተይዛ በሙስና ተከሳ ከ 5 ወር በላይ በእስር ያሳለፈችው የትግራይ ተወላጇ ሰላም በሪሁ፤ በቅርቡ የአማራ ክልል የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ ሆኖ በተሾመው በሌለኛው የትግራይ ተወላጅ ፍስሀ ወልደሰንበት ትዕዛዝ ከእስር እንድትፈታ መደረጓን ምንጮች ገልጸዋል።
የመረጃ ሠራተኛዋ ወይዘሮ ሰላም በሪሁ በፈጸመችው ወንጀል ከፖሊስነት ሥራዋ የተሰናበተች ቢሆንም አሁንም በፌዴራል መረጃና ደህንነት ቢሮ ውስጥ መመደቧ ታውቋል።
በቢሮው ውስጥ የወይዘሮ ሰላም ዋነኛ ሥራ ስለከተማው ነጋዴዎችና ወጣቶች ስለላ ማድረግና መረጃ ማቅረብ መሆኑን የጠቆሙት የቢሮው ምንጮች፤ ጉዳይ ለማስፈጸም ወደ ቢሮው የሚመጡም ሆነ የከተማው ነዋሪዎች ከእንዲህ ዓይነቶቹ ሰላዮች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሣስበዋል።