ሰኔ ፲፫( አሥራ ሦስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ባለፈው ወር የዶ/ር መረራ ጉዲና ጠበቃ በዶ/ር መረራ ላይ የቀረበው ክስ ከኢሳት እና ኦኤምኤን ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ክስ ጋር ተለይቶ እንዲታይ ጠይቆ ነበር። አቃቢ ህግ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለውን አስተያየት በጽሁፍ ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል። ፍርድ ቤቱም በጉዳዩ ላይ ለመወሰን ለሰኔ 30 ቀን 2009 ዓም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ፍርድ ቤቱ የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥንና የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ አድራሻቸውንና መቼ እንደተቋቋሙ ገልጾ እንዲያቀርብ ላቀረበው ጥያቄም፣ አቃቤ ሕግ በጽሁፍ ምላሽ ሰጥቷል።
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር መረራ ጉዲና እና ሁለቱም የሳተላይት ቴሌቪዥን ጣቢያዎች በአንድ ፋይል የሽብር ክስ ቀርቦባቸዋል። አቃቤ ሕግ በበኩሉ ዶ/ር መረራ ሕገመንግስቱን በሃይል ለመናድ ተቃውሞዎችን አነሳስተዋል በማለት ያቀረቡት የክስ መቃወሚያን ፍርድ ቤቱ ውድቅ እንዲያደርግ ሲል ጠይቋል። ኢሳት፣ ኦኤምኤን፣ ፕ/ሮ ብርሃኑ ነጋ እና አቶ ጃዋር መሀመድ የሽምቅ ውጊያ የሚያካሂዱ አሸባሪዎች እንዲሁም በዘረኝነት ላይ የተሰማሩ መሪዎች ናቸው ሲል አቃቤ ሕግ ለችሎቱ ገለጿል።
ዶ/ር መረራ ጉዲና የአውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ በጋበዛቸው ስብሰባ ላይ ተሳትፈው ወደ አገራቸው ሲመለሱ በኮማንድ ፖስቱ ከሕግ አግባብ ውጪ ከመኖሪያ ቤታቸው ከጓደኛቸው ጋር ተይዘው መታሰራቸው ይታወሳል።