ሰኔ 9 ፥ 2009
የሽብር ወንጀል ፈጽማችኋል በሚል በተለያዩ የክስ መዝገቦች በወህኒ ቤት ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ውስጥ በእነ መቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን የክስ መዝገብ የጥፋተኘነት ውሳኔ ተሰጠ። ከ13ቱ ተከሳሾች 7ቱ የጥፋተኝነት ውሳኔ ሲተለለፍባቸው፣ 6ቱ በነጻ እንዲሰናበቱ ተወስኗል። ይህ በእንዲህ እንዳለም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታሰሩ ዳንዔል ሺበሺና ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩ እንዲከላከሉ ፍ/ቤት ወሰነ።
ከግንቦት 7 ጋር በተየያዘ ክስ የተመሰረተባቸውና በአሸባሪነት ተወንጅለው ለአመታት ወህኒ ከቆዩት 13 ተከሳሾች 7ቱን ማለትም በላይነህ ሲሳይ፣ አለባቸው ማሞ፣ ቢሆነኝ አለነ፣ ፈረጃ ሙሉ፣ አትርሳው አስቻለው፣ አንጋው ተገኝና፣ አባይ ዘውዱ የጥፋተኝነት ውሳኔ ተላልፎባቸዋል። የጥፋተኝነት ውሳኔ ለመስጠትና የእስራት ዘመኑን ለመወሰን ለሰኔ 16 ፥ 2009 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት በተመሳሳይ የክስ መዘገቡ ያሉትን ተከሳሾች ከክሱ ነጻ ያደረጋቸው ሲሆን፣ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ግዜ ድረስ ስለመፈታታቸው የታወቀ ነገር የለም።
በነጻ እንዲሰናበቱ የተወሰነላቸው 6ቱ ተከሳሾች የመቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን፣ አወቀ ሞኝ ሆዴ፣ ተስፋዬ ታሪኩ፣ ተረፈ ፈንታሁን፣ እንግዳው ቃኘው፣ አግባው ሰጠኝ ሲሆኑ፣ አግባው ሰጠኝ የቂሊንጦ ወህኔ ቤትን በማቃጠል በሌላ የወንጀል ክስ ውስጥ ስሙ በመካተቱ ከእስር እንደማይለቀቅ ተመልክቷል።
በእነ መቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን የክስ መዝገብ ውስጥ የተዘረዘሩት ተከሳሾች፣ በኢትዮጵያ ሰላማዊ ፖለቲካ ትግል ውስጥ አስተዋጽዖ ሲያደርጉ የነበሩና ለህዝብ ነጻነት ተሟጋች ተብለው የሚጠቀሱ ይገኙባቸዋል።
በዚህ ረገድ አቶ ተስፋዬ ታሪኩ፣ ከመላው አማራ ህዝብ ድርጅት በኋላም ከመኢአድ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘም በምስራቅ ጎጃም በብርቱ አደራጅነቱ ይጠቀሳል።
ከቅንጅት አመራሮች ጋርም ለሁለት አመታት ያህል ታስሮ ከተፈታ በኋላ፣ እንደገና ወደ ወህኒ መጋዙንም ማስታወስ ተችሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተያያዘ ለወራት ያለክስ ታስረው የቆዩትና በቅርቡ ክስ የተመሰረተባቸው አቶ ዳንዔል ሺበሺና ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩ እንዲከላከሉ ተወስኖባቸዋል።
የአንድነት ፓርቲ አመራር በቀደመ ክሱ ይግባኝ ስለቀረበባት፣ በሌላ መዝገብ ፍ/ቤት በመመለስ ላይ መሆኑን መረዳት ተችሏል።
ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩ በተለያዩ ጋዜጦችና መጽሄቶች ላይ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በድፍረት የሚጽፍና የሚሳተፉ ጋዜጠኞች ሲሆን፣ የህትመት መድረኮች ሲዘጉም በማህበራዊ መድረኮች ንቁ ተሳታፊ እንደነበሩም ማስታወስ ተችሏል።