ኢሳት (ሰኔ 8 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ የከባቢ አየር ጸባይ ሙቀት መጨመር ለወባ በሽታ መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋጽዖ እያደረገ እንደሆነ አንድ ጥናት አመለከተ። በዝቅተኛና ሞቃታማ ቦታዎች ይራቡ የነበሩ የወባ በሽታ አስተላላፊ ትንኞች በሙቀቱ ምክንያት ህዝብ በብዛት ወደሚኖርባቸው ቀዝቃዛና ደጋማ የነበሩ ቦታዎች በመዛመት ላይ መሆናቸውን ጥናቱ አመልክቷል።
በሜይን ዩኒቨርስቲና በኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ አለም አቀፍ የአየርጸባይና የማህበረሰብ ጥናት ኢንስቲቲዩት ትብብር የተደረገው ይኸው ጥናት እንዳመለከተው አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ በከፍተኛ መልከ አምድር እንደሚኖር የተገለጸ ሲሆን፣ ቀዝቃዛውና ከፍተኛው የኢትዮጵያ መልከዓምድር ለወባ በሽታ መስፋፋት ምቹ እንዳልነበረ ይኸው ጥናት አመልክቷል። ይህ አካባቢም የተፈጥሮ የወባ በሽታ የሌለበት አካባቢ ሆኖ ያገለግል እንደነበር ጥናቱ አመልክቷል።
ሆኖም በከባቢ አየር ሙቀት በመጨመር ምክንያት በዝቅተኛና ቆላማ አካባቢዎች ይገኙ የነበሩት የወባ ትንኞች ህዝብ በብዛት ወደሚኖርባቸው ወደ ከፍተኛ ቦታዎች እየተስፋፉ እንደመጡ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ ተገልጿል።
ዶ/ር ብራድፊልድ ልዮን የተባሉ የዚህን ጥናት በሃላፊነት የመሩት የማየን ዩኒቨርስቲ የምርምር ፕሮፌሰር እንደተናገሩት፣ የወባ በሽታን የሚያመጡትን ፕላዝሞዲየም ፋልሲፋረም እና ፕላዝሞዲየም ቫይቫክስ ከ 18 ዲግሪ ሴንቲግሬድ እና 15 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በታች ሙቀት በሆኑ አካባቢዎች እንደማይራቡ ጥናቱ አመልክቷል። ዝቅተኛ ሙቀት የወባ በሽታ ተሸካሚ ትንኝ እንዳይራባ ያደርጋል ሲሉም ለመገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል። አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚኖርባቸው ከፍተኛ ቦታዎች ከ 1500-2500 ሜትር ከባህር ጠለል በላይ ያሉ ሲሆኑ፣ የወባ ተሸካሚ ትንኝ የማይገኙባቸው መሆኑም በጥናቱ ተጠቅሷል።
ሆኖም ዶ/ር ብራድፊልድ እንዳሉት አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ቦታዎች ከተጠቀሱት የሙቀት መጠኖች በታች ሙቀት ቢኖራቸውም፣ ከጊዜ ብዛት አኳያ ግን የእነዚህ አካባቢዎች ሙቀት እየጨመረ በመምጣቱ የወባ ትንኝ በሽታ የመስፋፋት ዕድሉን ከፍ ያለ እንደሆነ ተናግረዋል። ጥናቱ በኢትዮጵያ የሙቀት መጠኑ በአስር አመት ውስጥ .22 ዲግሪ ሴንቲግሬድ እየጨመረ እንደሚገኝ ጥናቱ አመልክቷል።
ኢንቫይሮመንታል ጆርናል በተባለ መጽሄት አርብ የታተመው ይህ ጥናት፣ በኢትዮጵያ በመቶ በሚቆጠሩ አካባቢዎች ላይ የሚታየውን የሙቀት መጠን ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ፣ የምልከታ ጥናት የታከለበትና የሳተላይትና የሌሎች የመረጃ ግብዓቶችን የተጠቀመ እንደሆነ ገልጿል።
ጥናቱ እኤአ ከ1981 እከ 2014 ማለትም ለ36 አመት ያክል ከተሰበሰበ ከፍተኛና ዝቅተኛ ሙቀት ጋር ተዳምሮ የተሰራ የምርምር ውጤት እንደሆነ ተገልጾ፣ በእነዚህ አመታት ለወባ በሽታ ምቹ የሆነው አካባቢ ከፍታ ከባህር ጠለል በላይ በ100 ሜትር የጨመረ ሲሆን፣ ለወባ ምቹ በሆነውና በተጋለጠው አካባቢዎች 100 ሜትር ከፍታ ውስጥ 6 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ይኖራሉ ሲል ያትታል።
የወባ በሽታ ስርጭት የራሱ ሂደት ያለውና ውስብስብ እንደሆነ የገለጹት በኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ በአለም አቀፍ የአየርጸባይና የማህበረሰብ ጥናት ኢንስቲቲዩት ባልደርባ ዶ/ር ማደሊን ቶምሰን፣ በእነዚህ አካባቢዎች የተከሰተው የሙቀት መጠን መጨመር ለአካባቢው ነዋሪዎች ስጋት ሆኖ መቀጠሉን ገልጿል።ሆኖም በእነዚህ አካባቢዎች የአየር ንብረት ሙቀት መጨመር የግድ የወባ በሽታ መጨመሩን የማያመለክት መሆኑን ጥናቱ አመልክቷል።
አዲሱ ጥናት ውስብስብ ጉዳዮችን ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ መሆኑን የጠቀሱት የስነአካባቢና የአየር ጸባይ ተመራማሪዎች፣ ጥናቱ የአካባቢ ሙቀት መጨመር የሚያመጣውን ተጽዕኖ በጥልቀት የዳሰደ እንደሆነ ገጸዋል።