ኢሳት (ሰኔ 8 ፥ 2009)
በጦርነት በምትታመሰው የመን የኮሌራ በሽታ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ መሆኑ ተገለጸ። በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ከ 940 ሰዎች በላይ በበሽታው መሞታቸው የታወቀ ሲሆን በሚቀጥሉት ጥቂት ወራትም ከ300 ሺ በላይ ሰዎች በላይ ሊያዙ እንደሚችሉ ተገልጿል።
በተበከለ ውሃና ምግብ በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰራጨ የሚገኘው የኮሌራ በሽታ፣ ባለፉት ሁለት ሳምንታት የስርጭት ሂደቱ ከሶስት እጥፍ በላይ በማደግ 5,400 አዳዲስ የበሽታው ተጠቂዎች መመዝገባቸው ታውቋል። ከበሽታው ተጠቂዎች ውስጥ 46 በመቶ የሚሆኑት ህጻናት መሆናቸው የሴቭ ዘ ችልድረን ሃላፊዎች ለመገናኛ ብዙሃ ገልጸዋል።
በየመን በኮሌራ በሽታ በቀን በአማካይ 30 ሰው እየሞተ መሆኑን ግብረሰናይ ድርጅቱ አስታውቋል።
በበሽታው ምክንያት በልጆቻቸው፣ በራሳቸው፣ እንዲሁም በባለቤቶቻቸው ላይ የሞት አደጋ ሊያጋጥም ይችላል በሚል እናቶች ፍርሃት ውስጥ እንደሚገኙ ዶ/ር ማሪያም የተባሉ ለሴብ ዘ ችልድረን የሚሰሩ ሃኪም ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ንጹህ የመጠጥ ውሃና በቂ ምግብ የማያገኙ የመናውያን 60 በመቶ እንደሚሆኑ የታወቀ ሲሆን፣ የተበከለ ውሃ የሚጠቀሙ፣ በምግብ እጥረት የተጎዱ እና በሽታ የመከላከል ሃይላቸው ዝቅተኛ የሆኑ ሰዎች የሞት አደጋ ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ተገልጿል።
በአገሪቱ የተከሰተው ጦርነት የኮሌራ በሽታ የመከላከል ሂደቱን እያስተጓጎለ እንደሚገኝ የተነገረ ሲሆን፣፣ አሁን በተከሰተው የኮሌራ በሽታ ከፍተኛ ተጠቂዎቹ ህጻናት መሆናቸውን በየመን የሴብ ዘ ችልድረን ሃላፊዎች መናገራቸው ተመልክተዋል።
በየመን 10 ሚሊዮን ህጻናትን ጨምሮ 70 በመቶ የሚሆነው ህዝብ የሰብዓዊ ዕርዳታ ፈላጊ መሆኑን የገለጸው ሪፖርቱ፣ አገሪቷ ወደ መበታተን አደጋ እያመራች እንደሆነ አመልክቷል።
ሆስፒታሎችና የኮሌራ በሽታን ለመከላከል የተቋቋሙ ማዕከላት በሽታውን ለመቆጣጠር የተቻላቸውን ሁሉ እያደረጉ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ሆኖም እነዚህ ማዕከላት መሰረታዊ መድሃኒትና የምግብ አቅርቦት እንደሌላቸው ተገልጿል።