ኢሳት (ሰኔ 8 ፥ 2009)
በቅርቡ ለአለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት የተመረጡት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም በዋሽንግተን ዲሲ ተቃውሞ ገጠማቸው። በዩ ኤስ አሜሪካ ርዕሰ መዲና ዋሽንግተን ዲሲ አለም ባንክ ጽ/ቤት ደጃፍ ተቃውሞ የቀረበባቸው የህወሃት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የአለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ የተቃውሞ ድምፅ እየተከተላቸው አካባቢውን ሲለቁ ታይተዋል።
ለአለም የጤና ድርጅት ዳይሬክተርነት በዕጩነት መወዳደራቸውን በመቃወም የተጀመረው ዘመቻ በተለይ በምርጫው የመጨረሻ ቀናት ተጠናክሮ እንደነበር ይታወሳል።
በተለይም የመጨረሻ ቀናት የዳይሬክተር ምርጫ ሲካሄድ በዋዜማው ለንደን ነዋሪ የሆነው አክቲቪስት ዘላለም ተሰማ ጄኔቭ ተገኝቶ በጉባዔው አዳራሽ ያካሄደው ተቃውሞ እንደነበር ይታወሳል።
ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖሞ በምርጫው ዳይሬክተር ሆነው መሰየማቸውን ተከትሎ፣ ተቃውሞ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አክቲቪስቶቹ መናገራቸው ይታወሳል።
ምርጫውን ተከትሎ አዲስ አበባ ሲገቡ በቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው ዶ/ር ቴዎድሮስ ለትግራይ ወጣቶች ባስተላለፉት መልዕክት የጠባቦችና የትምክህተኞች ጫጫታ አሸንፈናል ብለዋል። የአቶ መለስ መንፈስ እንደሚቀጥልም አጽንዖት ሰጥተዋል።
በሃገር ቤት ጥሩ አቀባበል የጠበቃቸው ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ ከምርጫው በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአገር በወጡበት በዋሽንግተን ዲሲ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል።
ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ከሁለት ሳምንት በኋላ እኤአ ጁላይ 1, 2017 በጄኔቭ ስራቸውን በይፋ ይጀምራሉ።