ኢሳት (ሰኔ 7 ፥ 2009)
በህወሃት የጦር መኮንንኖች የሚመራው የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ (ሜይቴክ) ላላከናወነው ግንባታ ከ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ክፍያ ተፈጸመለት።
በህወሃት የጦር ጄኔራሎች የበላይ አዛዥኘት ክፍያውን የወሰደው ሜቴክ ከ 3 አመት በፊት ግንባታውን አጠናቅቆ ለማስረከብ ውል ስለተፈረመበት ያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ መሆኑ ከዋና ኤዲተሩ የተገኘው መረጃ አመልክቷል። ሜቴክ ማዳበሪያ ፋብሪካውን ሰርቶ በማጠናቀቅ ማስረከብ የነበረበት በ 2006 አ’ም ቢሆንም አስከ አሁን ድረስ ሰርቶ ያጠናቀቀው ከግማሽ በታች (42 በመቶ ) ብቻ መሆኑን የኦዲት ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል’።
የዋናው ኤዲተር ሪፖርት አንዳመላከተው ሜቴክ ምንም አንኳን የአፈጻጻም ደረጃው ክፍያ ሊያስገኝለት የሚችለው 3.7 ቢሊዮን ብር ያህል ቢሆንም የተከፈለው 5.7 ቢሊዮን ብር መሆኑን እና ላልተከናወነ ስራ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ መከፈሉን አረጋግጧል። ዋና ኦዲተሩ አያይዞ አንደገለጸው ሜቴክ በገባው ውል መሰረት ከ 3 አመት በፊት አጠናቅቆ ማስረከብ ያለበትን የያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ በማንጓተቱ ምክንያት ኮርፖሬሽኑ ከባንክ ለተበደረው ብድር ወለድ ብቻ ከ 1.8 ቢሊዮን ብር በላይ መክፈሉን አስታውቀዋል።
በቀጣይም ሜቴክ በገባው ውል መሰረት ፕሮጀክቱ በተራዘመ ቁጥር የማዳበሪያ ፋብሪካው የሚያመነጨው ገቢ ስለማይኖር ለባንክ የሚከፈለው ወለድ በከፍተኛ መጠን ሊያድግ እንደሚችልና የፋብሪካው ዘላቂነት አደጋ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል አመላክተዋል።
በህወሐት የጦር መኮንንኖች የበላይ አዛዥነት የሚንቀሳቀሰው ሜቴክ በርካታ ፕሮጀክቶች ያለአቅሙ በመውሰድ በህዝብ ገንዘብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አያደረሰ መሆኑን በተደጋጋሚ የሚገልጽ መሆኑ የሚታወስ ነው ።