ሰኔ ፯ (ሰባት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በጉራጌ ዞን ዋና ከተማ ወልቂጤ ባለፈው ቅዳሜ ምሽት ላይ አንድ የቀቤና ብሄረሰብ ተወላጅ የሆኑ ሴት መገደላቸውን ተከትሎ አቶ መስፍን አዳነ የተባሉ የአማራ ብሄር ተወላጅ በጥርጣሬ ከተያዙ በሁዋላ በቡድን የተደራጁ ሰዎች ወደ እስር ቤት ገብተው ግለሰቡን የገደሉት ሲሆን፣ ፖሊሶች ቆመው እያዩም መኖሪያ ቤቱ እንዲቃጠል ተደርጓል።
የአካባቢው ፖሊሶች እጃቸው እንዳለበት የሚያመለክቱ መረጃዎች መኖራቸውን የሚገልጹት ምንጮች፣ ነገ ሃሙስ የዞኑን የቀቤና ተወላጆች በማነሳሳት የአማራ ተወላጆች ከአካባቢያችን ለቀው ይውጡ የሚል ጥያቄ እንዲያቀርቡ የቅስቀሳ ስራ እየሰሩ ነው ብለዋል።
ምንጮች እንደገለጹት በነፍስ ግድያ ተጠርጥሮ የተያዘው አቶ መስፍን ፣ በግድያው እጁ እንደሌለበት እየገለጸ እንዳይገደል ቢማጸንም ከሞት አላመለጠም። በፖሊስ ጥበቃ ስር ያለ ግለሰብ በተደራጁ ሰዎች እንዲገደል ሲደረግ ፖሊሶች ቆመው መመልከታቸው፣ ከግድያው ጀርባ የመንግስት እጅ እንዳለበት የሚያሳይ ነው በማለት ነዋሪዎች ገልጸዋል። በአሁኑ ሰአት ከፍተኛ ውጥረት መኖሩን የሚናገሩት ምንጮች፣ ውጥረቱ እንዲበርድ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ይገባቸዋል ብለዋል።
ወደ ስቱዲዮ ከገባን በሁዋላ የሟቹን የቅርብ ዘመድ ለማነጋገር የቻልን ሲሆን፣ ግለሰቡ የተገደሉት ወልቂጤ ፖሊስ ጣቢያ ላይ ነው ብለዋል። ፖሊሶች “ አማራ ነው የገደለን በማለት ገጠር ድረስ ህዝቡን ቀስቅሰውና አናሳስተው ማምጣታቸውንና እርምጃውን መውሰዳቸውን የሟቹ ዘመድ ተናግረዋል።
በ1983 ዓም በተመሳሳይ መንገድ ግጭት ተነስቶ እንደነበር የሟቹ ዘመድ ገልጸዋል