ኢሳት (ሰኔ 6 ፥ 2009)
የአርበኞች ግንቦት ሰባት የኢትዮጵያን ሃገራዊ አንድነትን ለማፈራረስ ከኦጋዴን ብሄራዊ ነጻ አውጪ ግንባር ጋር የጀመረው ሴራ በሚል የኢትዮጵያው አገዛዝ የፕሮፓጋንዳና የስለላ ተቋማት ዘጋቢ የቴሌቪዥን ፕሮግራም እያዘጋጁ መሆኑን ለኢሳት የደረስ መረጃ አመለከተ።
ዘጋቢ የቴሌቪዥን ፕሮግራሙ አርበኞች ግንቦት 7 በዚሁ ምክንያት እየፈረራሰና አባላቱም እጅ እየሰጡ ናቸው የሚሉ ቃለ-ምልልሶችና ፊልሞች እየተቀናበሩለት መሆናቸውን የኢሳት የትምህርት ብልጭታ አዘጋጅ ዶ/ር ታደሰ ብሩ መረጃውን መሰረት በማድረግ ማብራሪያ ሰጠዋል።
የቴሌቪዥን ፕሮግራሙን የሚያዘጋጁት የጸረ-ሽብር እና ፌዴራል ፖሊስ ጥምር ግብረ ሃይል ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) እና ኢኤንኤን ከተባለው አዲሱ የህወሃት ቴለቪዥን ጋር በመተባበር መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
የኢትዮጵያ አገዛዝ የፕሮፓጋንዳ ሰዎች እና የደህንነቱ አካላት ሰሞኑን የተጠመዱበት ስራ አርበኞች ግንቦት ሰባት እየፈራረሰና አባላቱም እየከዱት ነው የሚል ሆኗል። ለዚህም ማሳያ ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት) በተቋቋመው ኢኤን ኤን በተባለው ቴሌቪዥን ይህንኑ የሚመለከት ዘገባ በተደጋጋሚ እየቀረበ ይገኛል።
ለዚህ ስራ መነሻ የሆነው ደግሞ አርበኞች ግንቦት ሰባት ከኦጋዴን ብሄራዊ ነጻ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) ጋር ለኢትዮጵያ አንድነት በጋራ ለመስራት መስማማታቸው የፈጠረው ስጋት መሆኑ ተገልጿል። ይህን ተከትሎም የአርበኞች ግንቦት ሰባት የኢትዮጵያ ሃገራዊ አንድነት ለማፈራረስ ከኦጋዴን ብሄራዊ ነጻ አውጪ ግንባር ጋር የጀመረው ሴራ በሚል የኢትዮጵያ አገዛዝ የፕሮፓጋንዳና የስለላ ተቋማት ዘጋቢ የቴሌቪዥን ፕሮግራም እያዘጋጀ መሆኑን ለኢሳት የደረሰው መረጃ አመልክቷል።
የኢሳት ትምህርት ብልጭታ አዘጋጅ ዶ/ር ታደሰ ብሩ እንደገለጹት የቴሌቪዥን ፕሮግራሙ በተለይም በፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ላይ ያነጣጠረ ነው ብለዋል።
እንደ ዶ/ር ታደሰ ገለጻ ከኦብነግ ጋር የሚደረግ ግንኙኑነት ፀረ-ኢትዮጵያ እና ጸረ ሶማሌ ክልል አድርጎ ለማሳየት የዘጋቢ ቴሌቪዥን ፕሮግራሙ በዚህ መልኩ ተቀርጿል። አገዛዙ ከዚህ ቀደም ከኦብነግ የተለያዩ አንጃዎች ጋር ህገ መንግስቱን ተቀብሉ እያለ ሲደራደርና የኢትዮጵያ ህዝብ ሰላም አውርደናል ሲል እንደነበር ግን ዶ/ር ታደሰ አውስተዋል።
ዶ/ር ታደሰ በህወሃት የፕሮፓጋንዳ ሰዎችና በደህንነት ተቋሙ እየተዘጋጀ ያለው የቴሌቪዥን ዘጋቢ ፕሮግራም ሌላም ተልዕኮ ዓላማ እንዳለው ገልጸዋል። አርበኞች ግንቦት 7 እየፈረሰና እና አባላቱ ጥለውት እየሄዱ ነው በሚል እየተዘጀ ያለው ቅንብርም ተጠቃሽ መሆኑን ተናግረዋል።
በህወሃት የፕሮፓጋንዳና እና የደህንነት ተቋማት የሚዘጋጀው የቴሌቪዥን ፕሮግራም ይዘት ዕርስ በርሱ የሚቃረን መሆኑን ዶ/ር ታደሰ ይናገራሉ። አንደኛው የአርበኞች ግንቦት 7 ጥንካሬን የሚያሳይ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ድርጅቱ ተዳክሟል የሚል መሆኑን ገልጸዋል። ፕሮግራሙ ከፕሮግራሙ ያለፈ ውጤት እንደማይኖረው ያሳይል ባይ ናቸው።
የቴሌቪዥን ዘጋቢ ፕሮግራሙ ኢ ኤን ኤን (ENN) ምክትል ስራ አስኪያጅ በሆነውና በአድርባይነቱ የሚታወቀው አንሙት አብርሃም የሚዘጋጅ መሆኑን ዶ/ር ታደሰ ብሩ ገልጸዋል።
ለኢሳት የደረሰው መረጃ እንደሚያመለክተው በአርበኞች ግንቦት ሰባት ላይ በማነጣጠር በህወሃት አገዛዝ የሚዘጋጀው የቴሌቪዥን ዘጋቢ ፕሮግራም 5 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቦለታል።