ሰኔ ፮ (ስድስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በጭልጋና መተማ ወረዳዎች የሚገኙ የነጻነት ታጋዮች ቤተሰቦች እየታደኑ በመታሰር ላይ መሆናቸውን ከአካባቢው የሚደርሱን መርጃዎች አመልክተዋል።የወልቃይት ጠገዴን የአማራ ማንነት ጥያቄን ተከትሎ በጎንደር የተነሳውን ህዝባዊ እንቅስቃሴ ለመጨፈለቅ የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ የወሰደው ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ በርካታ አርሶአደሮች ቤተሰቦቻቸውን እየተዉ ጫካ ገብተው እየታገሉ ናቸው።
እነዚህ ታጋዮች በተለያዩ ጊዜያት የሚፈጽሙዋቸውን ጥቃቶች ተከትሎ አገዛዙ የታጋዮችን እንቅስቃሴ ለማቆም የተለያዩ የሃይል እርምጃዎችን ቢወስድም አልተሰካላትም። የተለያዩ የሃይማኖት አባቶችን በመጠቀም፣ የሽምግልና ጥረት ቢያደርግም ታጋዮቹ በያዙት ጠንካራ አቋም የተነሳ ሊሳካላት አልቻለም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የታጋዮችን ቤተሰቦች ማሰሩን እንደአማራጭ በመውሰድ በርካታ ሰዎችን አፍኖ ወስዷል።
ገብረህይወት ማሞ፣ አበረ ገብሬ፣ ማለዳ ከፋለ፣ አያል ጋርዴ፣ አማረ አካቪ እንዲሁም ታየው ገብሬ የተባሉት ሰዎች ጭልጋ እስር ቤት ታስረው የሚገኙ ሲሆን፣ ሌሎችም በርካታ ሰዎች እየታደኑ ነው። በርካታ አርሶአደሮች በመታሰራቸውም መታረስ የነበረባቸው የእርሻ ማሳዎች ሊታረሱ አልቻሉም።
የአካባቢው ነዋሪዎች የኢትዮጵያ ህዝብ ከታሳሪዎች ቤተሰቦች ጎን በመቆም የእርዳታ እጁን እንዲዘረጋም ጠይቀዋል።