ሰኔ ፮ (ስድስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ በጥቅምት ወር ላይ የተጣለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ፣ አሁንም በማንኛውም ጊዜ ህዝባዊ አመጽ ሊከሰት ስለሚችል ዜጓቿ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይጓዙ ፣ ከተጓዙም ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስቧል።
የኢትዮጵያ መንግስት መጋቢት ወር ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማራዘሙን የገለጸው የአሜሪካ መንግስት፣ አሁንም ድረስ አለመረጋጋት መኖሩን በተለይም በባህርዳርና ጎንደር ከተሞች ጎልቶ እንደሚታይ ገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሚ ኢንተርኔት፣ የሞባይል ዳታና የስልክ አገልግሎት እየዘጋና እያፈነ መሆኑ፣ አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኢምባሲ በኢትዮጵያ ከሚገኙ አሜሪካውያን ጋር ለመገናኘትና ምክር ለመስጠት መቸገሩን እንዲሁም የቆንስላ አገልግሎት ለመስጠት መቸገሩንና እንቅስቃሴውን መቀነሱን ገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግስት የአሜሪካ ዜጎች ኢትዮጵያ ውስጥ ሲታሰሩ እንኳን ለኢምባሲው አያሳውቅም ሲል ወቀሳ አቅርቧል። ዜጎቹ ህዝብ በብዛት በተሰበሰበባቸው እና በሰላማዊ ሰልፎች መሃል እንዳይገኙ፣ በየጊዜው አካባቢያቸውን እንዲቃኙ የመከረው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያቤት፣ መንግስት ሰላማዊ ሰልፎችን ለመበትን ሲል በቀጥታ እንደሚተኩስ፣ ሃይል እንደሚጠቀም እንዲሁም ሰላማዊ የሆነን የተቃውሞ ሰልፍ ያለምንም ማስጠንቀቂያ የሃይል እርምጃ በመውሰድ ወደ ሃይል ሊለውጠው እንደሚችል ኢምባሲው ለዜጎቹ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
አሁን ያለው የደህንነት ሁኔታ አስተማማኝ ባለመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ አሜሪካውያን ስልክ ቁጥሮቻቸውን እንዲያስመዘግቡም አገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አሳስቧል።
ገዢው ፓርቲ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዳመጣ በተደጋጋሚ ቢገልጽም፣ አንድም የውጭ አገር መንግስት አልተቀበለውም። አሜሪካና እንግሊዝን ጨምሮ በርካታ አገሮች ቀደም ብሎ ያውጡዋቸውን የጉዞ ማስጠንቀቂያዎች አልቀየሩም።
የአሜሪካ መንግስት የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት መግለጫ፣ በአገሪቱ ሰላም እንደሰፈነ አድርጎ በርካታ የቅስቀሳ ስራ እየሰራ ላለው የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ ትልቅ የራስ ምታት እንደሚፈጥርበት ዘጋቢያችን አስተያየቱን አስፍሯል።