ሰኔ ፭ ( አምስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት በአዊ ዞን ቲሊሊ ከተማ የፖሊስ አዛዥ የሆነው ኮማንደር አወቀን ጨምሮ አንድ የፖሊስ መኮንንና ሌላ አንድ የወረዳ የካቢኔ አባል ታስረዋል።
አንዳንድ ፖሊሶቹ የታሰሩት ባለፈው አርብ ከሰአት በሁዋላ ስብሰባ ጨርሰው ከወጡ በሁዋላ በቤታቸው ውስጥ ሲሆን፣ ኮማንደር አወቀ ደግሞ ስራ ቦታው ላይ መያዙን ታውቋል።
የፖሊስ አባላት መስራት ያለባቸው ለአማራ ህዝብ እንጅ ለሌላ ለማንም መሆን የለበትም በማለቱና በፖሊስ መምሪያው ውስጥ ያሉ አባላት ላይ ብሄርተኝነት እንዲስፋፋ አድርጓል ተብሎ ነው። ከዚህ ቀደም በከተማው ተነስቶ በነበረው ህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ወቅት፣ ኮማንደሩ በትግራይ ተወላጆች ላይ እርምጃ እንዲወሰድባቸው አስደርጓል የሚል ውንጀላም ቀርቦበታል። ይሁን እንጅ በህወሃት የሚመራው ኮማንድ ፖስት የሚባለው ወታደራዊ ገዢው ቡድን የፖሊሶችን ስራ ተክቶ እየወሰደ ያለው እርምጃ፣ በክልሉ ፖሊሶች ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም። የክልሉ ፖሊሶች ከጨዋታ ውጭ ያደረጋቸውን ኮማንድ ፖስት አሰራር በተደጋጋሚ ሲቃወሙት ከርመዋል።
በክልሉ ጸጥታ ዘርፍ ውስጥ የሚሰሩ ከፍተኛ የመረጃ ሰራተኞች ላይ እርምጃ ለመውሰድ መታቀዱንም ለኢሳት የደረሰው መረጃ ያመለክታል።
ከክልሉ ዜና ሳንወጣ በ ሰሜንና ደቡብ ጎንደር የሚገኙ የአካባቢውን ወጣቶች ያስተባብራሉ የተባሉ ወጣቶች በህወሃት የደህንነት ሃይሎች እየታፈኑና እየተገደሉ መሆኑን የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ። በደብረታቦር ከተማ ሰኔ 3 ቀን 2009 ዓም ከምሽቱ 3 ሰዓት መኩሪያ ኃይሌና ደነቀው ደጀኔ የተባሉ ወጣቶች የተገደሉ ሲሆን፣ ወጣቶቹ በሰው እንደተገደሉ ተደርጎ መቅረቡን የአካባቢው ምንጮች ገልጸዋል። በጎንደር ከተማ ደግሞ ወጣቶችን የጦር መሳሪያ ታስታጥቃላችሁ የተባሉ 3 ሰዎች ታፍነው መወሰዳቸውን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
በሌላ በኩል ደግሞ በሰሜን ወሎ ዞን የካቢኔ አባላት ላይ ጠንካራ ነው የተባለ ግምገማ ተካሂዷል። ግምገማውን ተከትሎ አቶ አህመድ የከተማ አገልግሎት ሃላፊ፣ አቶ በረደድ ተሰማ፣ የትምህርት መምሪያ ሀላፉ፣ አቶ ፀሀዬ መንገሻ ፣ የወልዲያ ከንቲባ የነበረ አሁን ትምህርት መምሪያ የተመደበ፣አቶ አራጌ የዞኑ ሲቪል ሰርቪስ መምሪያ ሀላፊ ከስራ ታግደዋል ።ባለስልጣኖቹ የታገዱበት ምክንያት ደመወዛቸው ከማይፈቅደው በላይ የቤት ግዥ የፈፀሙ እንዲሁም በተለያዩ ሰዎች ስም የከተማ ቦታዎችን ይዘዋል በሚል ነው። አቶ ጸሃየ መንገሻ ከ10 በላይ ቦታ በዘመድ አዝማድ መውሰዳቸው ተነግሯል።