ኢሳት (ግንቦት 30 ፥ 2009)
የግብጽ ባለስልጣናት በመገንባት ላይ ያለው የአባይ ግድብ ውሃ መሙላት በሚጀምርበት የጊዜ ሰሌዳ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ድርድር እየተካሄደ መሆኑን ገለጹ።
የሃገሪቱ ባለስልጣናት ከዚህ በፊት በሁለቱ ሃገራት መካከል ሲካሄድ በቆየ ድርድርና ስምምነት ወቅት ግድቡን በውሃ የመሙላቱ ሂደት እንዲዘገይ ጥያቄን ሲያቀርቡ መቆየታቸው ይታወሳል። የግብፅ ባለስልጣናት ግድቡ በታችኛው ተፋሰስ ሃገራት ላይ የሚያመጣው ተፅዕኖ በጥናት ተደግፎ እስኪቀርብ ድረስ የግድቡ የግንባታ ሂደት ለተወሰነ ጊዜ እንዲዘገይ ሃሳብ አቅርበዋል።
በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ ከኢትዮጵያ በኩል የተሰጠ ዝርዝር መረጃ ባይኖርም የግብፅ ባለስልጣናት ግድቡ በውሃ መሙላት በሚጀምርበት የጊዜ ሰሌዳ ዙሪያ ድርድር እየተካሄደ መሆኑን እንደገለጹ አል አህራም የተሰኘ ጋዜጣ ዘግቧል።
ኢትዮጵያ እና ግብፅ በአባይ ግድብ ግንባታ ዙሪያ ያላቸው አለመግባባት ለመፍታት 14 ድርድሮችን ያካሄዱ ቢሆንም፣ እስከ አሁን ድረስ የተደረሰ የመጨረሻ ስምምነት አለመኖሩን ለመረዳት ተችሏል።
ኢትዮጵያና ግብፅ ሱዳንን በማካተት ግድቡ በታችኛው ተፋሰስ ሃገራት ላይ የሚያመጣው ተፅዕኖ በሁለት የፈረንሳይ ኩባንያዎች እንዲካሄድ ባለፈው አመት ስምምነት መድረሳቸው የሚታወስ ነው። ጥናታቸው እያካሄዱ ያሉት ሁለቱ ኩባንያዎች የመጀመሪያ ዙር የጥናት ግንባታቸው ለሃገራቱ እንዳቀረቡም ታውቋል።
ይሁንና የግብፅ ባለስልጣናት ለሶስቱ ሃገራት በቀረበው የጥናቱ ውጤት ዙሪያ ለመገናኛ ብዙሃን መረጃን ከመስጠት ተቆጥበዋል።
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ፣ የግብፅና ሱዳን የቴክኒክ ባለሙያዎች ቡድን በሁለቱ የፈረንሳይ አጥኚ ቡድኖች የቀረበውን የጥናት ውጤት እየተመለከቱት እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል።
በፈረንሳይ ኩባንያዎቹ እየተካሄደ ያለው የጥናት ውጤት ይግባኝ የሌለው ሲሆን፣ ኩባንያዎቹ ጥናቱን ለማካሄድ እስከ ስምንት ወር እንደሚፈጅባቸው ሲገለጽ ቆይቷል።
ሶስቱ ሃገራት ለሁለቱ የፈረንሳይ ኩባንያዎች አምስት ሚሊዮን ዩሮ ክፍያውን የፈጸሙ ሲሆን፣ ተቋማት በቀጣዮቹ ጥቂት ወራት ውስጥ የመጨረሻ የጥናት ውጤታቸውን ለሃገሪቱ ያስረክባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያና ግብፅ በአባይ ግድብ የውሃ መሙላት የጊዜ ሰሌዳ ዙሪያ እያካሄዱ ያለው ድርድር ከመጀመሪያ ዙሪያ ጥናቱ መቅረብ ጋር ግንኙነት ይኑረው አይኑረው የታወቀ ነገር የለም።