ኢሳት (ግንቦት 30 ፥ 2009)
የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ምክር ቤት በኢትዮጵያ ሃሳባቸውን በተለያዩ መንገዶች የሚገልጹ ሰዎች ለእስር መዳረግና የሚተላለፍባቸው የእስር ቅጣት እንዳሳሰበው ገለጸ።
በቅርቡ በኢትዮጵያ ጉብኝት አድርገው ወደ ኦሮሚያ ክልል እንዳይጓዙ የተደረጉት የምክር ቤቱ ሃላፊ ዘይድ ራ’ድ አልሁሴን፣ ለመንግስት ገለልተኛ ምርመራ በሃገሪቱ ለማካሄድ ያቀረቡት ጥያቄ አሁንም ድረስ ምላሽ አለማግኘቱን አስታውቀዋል።
ምክር ቤቱ በስዊዘርላንድ ጀኔቭ ከተማ እያካሄደ ባለው ጉባዔ ሪፖርትን ያቀረቡት የምክር ቤቱ ሃላፊ በቅርቡ በቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር በነበረው ዮናታን ተስፋዬ ላይ የተላለፈ ፍርድ በዋቢነት አውስተዋል።
ዮናታን ተስፋዬ በተለያዩ ጊዜያት በማህበራዊ ድረገ-ጾች ላይ ባሰፈረው አስተያየቶችና ጽሁፎች አመጽን አነሳስቷል የሚል ክስ ተመስርቶበት በቅርቡ የስድስት አመት ከስድስት ወር የእስር ቅጣት እንደተላለፈበት ይታወሳል።
ይህንኑ ጉዳይ በዋቢነት በጉባዔው ያነሱት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤቱ ሃላፊ ዘይድ ራድ በሃገሪቱ ሃሳብን በነጻነት በመግለጻቸው ብቻ ለእስር የሚዳረጉና የእስር ቅጣት የሚተላለፍባቸው ድርጊት አሳስቧቸው እንደሚገኝ መግለጻቸውን ኢንተር ፕሬስ ሰርቪስ የተሰኘ የዜና አውታር ዘግቧል።
ከአንድ አመት በፊት በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የደረሰውን ግድያና እስራት ለመመርመር የሰብዓዊ መብት ምክር ቤቱ ጥያቄ ቢያቀርብም በመንግስት ፈቃድ መከልከሉ ይታወሳል።
የምክር ቤቱ ሃላፊ ዘይድ ራድ ጥያቄውን በድጋሚ መቅረቡንና በቀጣዩ አመት ለተመሳሳይ ጉዳይ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚጓዙም በጉባዔው ገልጸዋል።
መንግስታዊው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባካሄደው ምርመራ 745 ሰዎች መገደላቸው ቢገለጽም፣ ሂውማን ራይስት ዎችን ጨምሮ በርካታ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ድርጅቶች ቁጥሩ ከዚህ የበለጠ ሊሆን እንደሚችል እየገለጸ ይገኛል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ምክር ቤት ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ቡሩንዲ፣ ቤንዙዌላ እንዲሁም ፊሊፒንስ በሃገራቸው የሰብዓዊ መብት ዳሰሳ እንዲካሄድ ጥያቄ ቢቀርብላቸው ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸው በልዩ ጉባዔው ኮንኗል።
አራቱ ሃገራት በአሁኑ ወቅት በምክር ቤቱ በአባልነት ታቅፈው የሚገኙ ሲሆን፣ አሜሪካ እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አካላት ምክር ቤቱ የሰብዓዊ መብት ረገጣ ፈጽመዋል በሚባሉ አባል ሃገራት ላይ ጠንካራ አቋምን እንዲከተል አሳሰበዋል።
በምክር ቤቱ በአባልነት የተወከሉ ሃገራት ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት መርሆዎች ተገዢ አለመሆናቸው ጥያቄ አስነስቶ እንደሚገኝም ከጄኔቭ የሚወጡ መረጃዎች አመልክተዋል።
የሁለት ሳምንት ጉባዔው ከሰኞ ጀምሮ በማካሄድ ላይ የሚገኘ ምክር ቤቱ በአለም ዙሪያ ስላሉ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች በመምከር የተለያዩ ውሳኔዎች ያስተላልፋል ተብሎ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ ከተያዘው የፈረንጆች አመት ጀምሮ ለሁለት አመት በምክር ቤቱ አባልነት መመረጧ የሚታወስ ነው።