ግንቦት ፳፱ ( ሃያ ዘጠኝ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በምእራብ ጎጃምና አዊ አስተዳደሮች ከፍተኛ የተምች ወረርሽኝ የተከሰተ ሲሆን፣ ወረርሽኙ ከእለት ዕለት በመስፋፋት በሁሉም አካባቢዎች የበቀሉ እጽዋትን በማውደም ላይ መሆኑን አርሶአደሮች ተናግረዋል። ገዥው መንግስት ተገቢውን የመከላከያ መድሃኒት አላቀረበልንም በማለትም ወቀሳ እያቀረቡ ነው።
በአንዳንድ ቀበሌዎች የቀረበው መድሃኒት የአገልግሎት ጊዜው ያለፈ ቢሆንም “ዝም ብላችሁ ተጠቀሙበት” የሚል ምላሽ በመስጠት ህብረተሰቡን ለጉዳት የሚዳርጉ መድሃኒቶችን ከመጋዝን በማውጣት እያከፋፈሉ መሆኑን የክልሉ ወኪላችን ገልጻለች።
መድሃኒቱን ለመርጨት የሚያስፈልጉ የአፍ መከለያ፣ቱታና የእጅ ጓንት የመሳሰሉ መገልገያዎች ባለመቅረባቸው በአርሶአደሮች ጤና ላይ በሂደት ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትልባቸው እንደሚችል በአካባቢው የሚሰሩ የግብርና ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡
የተምቹ ተፈጥሮ በቶሎ የመራባት እና ካደገ በኋላ በመብረር በቀላሉ አካባቢውን የሚበክል ቢሆንም፣ የገዥው መንግስት አመራሮች የመከላከያ መድሐኒቱን ከማቅረብ ይልቅ አርሶ አደሮች በእጃቸው እየለቀሙ እንዲያቃጥሉ ሲያዙ መታየታቸው ለጉዳዩ ትኩረት አለመስጠጣቸውን እንደሚያሳይ ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡
የምዕራብ ጎጃም እና የአዊ አካባቢዎች የሃገሪቱን ከፍተኛ የሰብል ምርት የሚሸፍኑ ሲሆን አካባቢው በመጤ ተምቹ ከተጠቃ በቀጣዩ ዓመት ከፍተኛ የምርት እጥረት ሊከሰት እንደሚችል ባለሙያዎች አስተያየታቸውን ለዘጋቢያችን ሰጥተዋል፡፡