ኢሳት (ግንቦት 28 ፥ 2009)
በፕሬዚደንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሚመራው የኤርትራ መንግስት በስልጣን ላይ እስካለ ድረስ የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት ሊሻሻል እንደማይችል ሌ/ጀኔራሊ ጻድቃን ገ/ተንሳይ ገለጹ። በኤርትራ ህዝብ ላይ የሚደርሰው ግፍና በደል ሲያበቃ ግንኙነቱ ጤናማ እንደሚሆንም ተስፋቸውን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ስለሚፈጸመውና አለም አቀፍ ተቋማት ጭምር ስለሚያጋልጡት የሰብዓዊ መብት ረገጣ ምንም ሳይጠቅሱ አልፈዋል።
በአንጋፋው የህወሃት ታጋይና የቀድሞ ጠቅላይ ኤታማጆር ሹም ጻድቃን ገ/ተንሳይ ከመንግስታዊው አዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ኤርትራ ከአረብ ሃገራት ጋር በፈጠረችው ግንኙነት የኢኮኖሚ ችግሩ እየፈታላት ነው በማለት ጉዳዩን በአሳሳቢነት ጠቅሰው፣ በዚህም የኤርትራ መንግስት ጡንቻን ያፈረጠመ ያህል ዋስትና እየተሰማው ነው በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል።
በኤርትራ ሳቢነትና በአረብ ሃገሮች ፍላጎት ከቀይ ባህር አካባቢ እየተነጠልን ነው በማለት አካባቢውን የቃኙት ጀኔራል ጻድቃን ገ/ተንሳይ ሳውዲ አረቢያ፣ ግብፅና የተባበሩት አረብ ኤመሬትስ በኤርትራ የጦር ሰፈር አቋቁመዋል ይባላል በማለትም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የኢሳያስ መንግስት እስካለ ድረስ አስቸጋሪ ሁኔታው ይቀጥላል በማለት የኤርትራ መንግስትና ፕሬዚደንት ኢሳያስ ለህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት ፈተና መሆናቸውን አመልክተዋል።
ከኤርትራ እየተነሱ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ የኢትዮጵያ መንግስት ተቃዋሚዎች የሻዕቢያ ተላላኪ በማለት የተጠቀሱት የቀድሞ ጄኔራልና አዲሱ የቢዝነስ ሰው ጻድቃን ገ/ተንሳኤ የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት ከኤርትራ ጋር በሚሰሩ ተቃዋሚዎች ላይ የሚያደርገውን ቁጥጥር እንደሚያጠናክርም ጥሪ አቅርበዋል።
የኤርትራ መንግስት ከኤርትራ ህዝብ ለመነጠል ስራዎችን መስራት ይገባል በማለት የተናገሩት ጻድቃን ገ/ተንሳይ፣ ከባድ ጊዜ የሚወስድ ቢሆንም ከኤርትራውያን ጋር በመሆን ወታደራዊ አቅምን ጭምር በመጠቀም የኤርትራ መንግስት ዕድሜ የሚያጥርበት ሁኔታ መስራት ይገባል ብለዋል።
ከኤርትራ መንግስት ጋር ጤናማ ግንኙነት ሊመሰረት ይችላል ወይ በሚል የተጠየቁት ጄኔራል ጻድቃን ገ/ተንሳይ ብዙ አድርገንለት ጀርባችንን በሳንጃ የወጋን መንግስት በመሆኑ የተለየ ነገር አልጠብቅም ብለዋል።
ከኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት ባሻገር በደቡብ ሱዳን እንዲሁም በጅቡቲ ያለው ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑንም የቀድሞ ጠቅላይ ኤታማጆር ሹም ገልጸዋል።
የጅቡቲ ጉዳይ በሃያሉ ሃገራት እጅ ሲገባ፣ በደቡብ ሱዳን ጉዳይም ኡጋንዳ፣ ሱዳንና ግብፅ ሚናቸው የጎላ መሆኑን በማመልከትም ችግሩ ዘርፈ ብዙ ሆኖ መውጥእቱ አብራርተዋል።
ሌ/ጀነራል ጻድቃን ገ/ተንሳዬ የህወሃት ታጋይ የነበሩ እስከ 1993 የህወሃት ክፍፍልም የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማጆር ሹም ነበሩ። በአሁኑ ወቅት በቢዝነሱ አለም የሚገኙ ሚሊዮነር ሲሆን፣ የራያ ቢራ መስራችና ከፍተኛ ባለድርሻ መሆናቸንም መረዳት ተችሏል።