ስድስት የአረብ ሃገራት ከኳታር ጋር የነበራቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን አቋረጡ

ኢሳት (ግንቦት 28 ፥ 2009)

ሳውድ አረቢያን ጨምሮ ስድስት የአረብ ሃገራት ኳታር አይሲስን ጨምሮ የተለያዩ ታጣቂዎችን ትደግፋለች በማለት ከሃገሪቱ ጋር ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አቋረጡ።

ሳውዲ አረቢያ፣ ግብፅ፣ የተባበሩት አረብ ኤመሬትስ፣ ባህሬን፣ የመን እና ሊቢያ ከኳታር ጋር ያላቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያቋረጡ ሃገራት ሲሆኑ፣ ሃገራቱ በሃገራቸው የሚገኙ የኳታር ዜጎች እንዲሁም ዲፕሎማቶች ሃገራቸውን በአስቸኳይ ለቀው እንዲወጡ መጠየቃቸውን ቢቢሲ ሰኞ ዘግቧል።

ሳውዲ አረቢያ ከኳታር ጋር የምትገኝባቸውን የምድር፣ የየብስና፣ የባህር ግንኙነት እንዲቋረጥ ማድረጓን የሳውዲ አረቢያ ዜና አገልግሎት የሃገሪቱ ባለስልጣናት ዋቢ በማድረግ በዘገባው አስነብቧል።

የሳውዲ አረቢያ መንግስት ኳታር በኢራን ከሚደገፉ ታጣቂዎች ጋር ንግኙነት በመፍጠር የተለያዩ ድጋፎችን ታደርጋለች ስትል ምክንያቷን ገልጻለች።

በባህሬን የተጀመረው ዕርምጃ በሰዓታት ልዩነት አምስት ሃገራትን ያስከተለ ሲሆን፣ ሳውዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤመሬትስና ፣ባህሬን የኳታር ዜጎች ከሃገራቸው በሁለት ሳምንት ውስጥ ለቀው እንዲወጡ ቀነ ገደብ አስቀምጠዋል።

የኳታር መንግስት እስካሁን ድረስ የወሰደው የአጸፋ እርምጃ ባይኖርም ሃገራቱ የወሰዱት ፍትሃዊ ያልሆነና መሰረተ ቢስ ነው ሲል ምላሽን ሰጥቷል።

የስድስት ሃገራት የአየር መንገዶች በበኩላቸው ወደ ኳታርም ሆነ ከኳታር የሚያደርጉትን የአየር በረራ አገልግሎት እንዳቋረጡም ታውቋል።

ሳውዲ አረቢያ የአረብ ሃገራትን በማሰባሰብ በየመን እያካሄደ ካለው ወታደራዊ ዘመቻ ኳታርን ያሰናበተች ሲሆን፣ የፖለቲካ ተንታኞች የሃገራት እርምጃ በቀጠናው አለመረጋጋትን ያሰፍናል ሲሉ ስጋታቸውን እየገለጹ ይገኛል።

በአይሲስ ላይ እየተካሄደ ያለውን ወታደራዊ ዘመቻ ከአሜሪካ ጎን በመቆም ድጋፍ እያደረገች እንደሆነ የሚነገርላት ኳታር፣ ከኢራቅ የሺአ አመራሮች ታጣቂ ቡድኑን በገንዘብ ትደግፋለች የሚል ቅሬታ ሲቀርብባት ቆይቷል።

ይሁንና የኳታር መንግስት የሚቀርብበትን ቅሬታ ሲያስተባብል የቆየ ሲሆን፣ የሃገሪቱ ባለሃብቶች ጭምር በሶሪያ ለሚገኙ የአይሲስ ታጣዎች በተለያዩ መንገዶች ድጋፍን ያደርጋሉ የሚል አቤቱታ ሲቀርባባቸው መቆየቱን ቢቢሲ በዘገባው አመልክቷል። የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሪክስ ቲለርሰን በበኩላቸው ከኳታር ጋር ዲፕሎማሲያዊ አለመግባባት ውስጥ የገቡት ሃገራት ልዩነታቸውን በድርድር እንዲመለከቱት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2022 የአለም ዋንጫን ለማዘጋጀት በዝግጅት ላይ የምትገኘው ኳታር፣ ሃገራቱ የወሰዱት ዕርምጃ  የዜጎቹን የዕለት ከእለት እንቅስቃሴ የሚጎዳ አይደለም ስትል አስታውቃለች። ይሁንና፣ ሃገሪቱ 40 በመቶ የሚሆነውን የምግብ ፍጆታዋን ከሳውዲ አረቢያ የምታስገባ በመሆኑ ከኳታር የምግብ እጥረት ሊከሰት ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።