የፌዴራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት በዶ/ር መረራ ጉዲና፣ በኢሳትና ኦኤምኤን ላይ የቀረቡ ክሶች እንዲሻሻሉ ብይን ሰጠ

ኢሳት (ግንቦት 28 ፥ 2009)

የፌዴራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት በዶ/ር መረራ ጉዲና እንዲሁም በኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) እና በኦሮሞ ሚዲያ ኔትዎርክ ላይ በአቃቤ ህግ የቀረቡ ክሶች እንዲሻሻሉ ብይን ሰጠ።

ጠቅላይ አቃቤ ህግ የመሰረተባቸውን ክስ መሰረት በማድረግ ዶ/ር መረራ ጉዲና የቀረበባቸው ክስ እንዲሻሻል ጥያቄን አቅርበው የነበረ ሲሆን፣ ተከሳሹ ክሳቸው በተናጠል እንዲታይ መጠየቃቸው ይታወሳል።

ይህንኑ ጉዳይ ሲከታተል የነበረው ፍርድ ቤቱ ከተከሳሹ ጋር ክስ የቀረበባቸው ኢሳት እኛ የኦሮሞ ሚዲያ ኔትዎርክ ክስም እንዲሻሻል ብይን መስጠቱን ሪፖርተር ጋዜጣ በዕሁድ እትሙ አቅርቧል። 

ፍርድ ቤቱ በሰጠው ብይን እንደገለጸው ሁለቱ የሚዲያ ተቋማት በየት ሃገር እንደሚገኙ፣ መቼና እንዴት እንደተቋቋሙ እንዲሁም ህጋዊ ስለመሆናቸው ተገልጾ መቅረብ ይኖርበታል ብሏል።

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተሰየመ ጊዜ ዶ/ር መረራ ጉዲና አቤቱታን ያቀረቡ ሲሆን፣ ከቀረቡባቸው ክሶች ጋር የደረሷቸው ማስረጃዎች የወንጀለኛ መቅጫ ስነስርዓት ህጉን የተከተሉ አመለሆናቸውን አስረድተዋል።

ዶ/ር መረራ ባልተከሰሱበት በሽብርተኝነት አዋጁ መሰረት የቀረቡ በመሆናቸው ተስተካክለው እንዲደርሷቸው ፍርድ ቤቱ እንዲያዝላቸው ጠይቅዋል።

ፍርድ ቤቱ ጥያቄውን የተቀበለ ሲሆን፣ አቃቤ ህግ አሻሽሎ የሚያቀርበውን ክስ ለመቀበልና ተከሳሹ ባቀረቡት አቤቱታ ላይ ብይን ለመስጠት ለሰኔ 13 ፥ 2009 አም ቀጠሮ መስጠቱ ታውቋል።