በኦሮሚያ ክልል የመጀመሪያ ደረጃ የአማርኛና የኦሮምኛ ቋንቋ ስርዓተ ትምህርቶች ክህሎት ስለማያጎለብቱ ክለሳ ሊደረግባቸው ነው ተባለ

ኢሳት (ግንቦት 28 ፥ 2009)

በኦሮሚያ ክልል ከአምስተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ከአምስት አመት በላይ በሁለተኛ ቋንቋነት ሲያገለግሉ የነበሩ የተማሪዎች የአማርኛ ቋንቋ መማሪያ መጻህፍት ክለሳ እንዲደረግባቸው መወሰኑን የክልሉ የትምህር ቢሮ ገለጸ።

በክልሉ ይሰጥ የነበረው የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት የተማሪዎችን የአማርኛ ቋንቋ ክህሎት በተገቢው ሁኔታ የማያጎለብትና የማያዳብር ሆኖ በመገኘቱ እንዲሻሻል መደረጉን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

ትምህርት ሚኒስቴር ከ5ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ላሉ አራት ክፍሎች ለእያንዳንዳቸው አንዳንድ የአማርኛ ቋንቋ መማሪያ መጽሃፍት የሚያዘጋጅ ሲሆን፣ ሶስት ሚሊዮን መጽሃፍት እንደሚታተም ታውቋል።

የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ የሆኑት ዶ/ር ቶላ በረሶ በክልሉ ከዚህ በፊት በተደረገ ጥናት ከ5ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች የማንበብና የመጻፍ ክህሎታቸው ዝቅተኛ ነው ሲሉ ለሪፖርተር ገልጸዋል። መጽሃፍቶቹን ለማተም አገር አቀፍና አለም አቀፍ ተቋማት በጨረታ ተሳታፊ ሆነው መቅረባቸውም ተመልክቷል።

አዲሶቹ የአማርኛ ቋንቋ መማሪያ መጽሃፍት ከ2010 አም ጀምሮ በተማሪዎች እጅ ይገባል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የተከለሱት አዳዲስ የቋንቋ መጽሃፍት ለማስተማር ሲባል በክረም ወቅት ከ60ሺ በላይ መምህራን ሰልጠነው ወደስራ የገባሉ ተብሏል።

ከ20 አመት በፊት ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘው የኦሮሚኛ  የአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት ስርዓት ቋንቋውን በተገቢው መልኩ ለመናገርና ለማስተማር ችግር አምጥቷል ተብሎ ክለሳ እንዲደረግበት ተወስኗል።

በቅርቡ በቋንቋ ላይ በተካሄደ ጥናት የአፋን ኦሮሞ ቋንቋ በማስተማርና በመናገር ላይ ችግሩ መኖሩ በመረጋገጡ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ሲሰጥ በቆየው ትምህርት ላይ ማስተካከያ እንዲካሄድ ውሳኔ መደረሱን የኦሮሚያ ቴሌቪዥን ጣቢያ የክልሉ የትምህርት ቢሮን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ቀድሞ በቁቤ ቋንቋ ትምህርት የሚጀምረው የ “ላ” ፊደል በ “ጋ” እንዲተካ መደረጉንና አዳዲስ የትምህርት መጽሃፍት እንዲታተሙ መደረጉን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል።

የቁቤ ትምህርት ከ1986 አም ጀምሮ በስራና በትምህርት አገልግሎት መጀመሩ ይታወሳል።