ኢሳት (ግንቦት 25 ፥ 2009)
በቀጣዩ ሳምንት ጠቅላላ ጉባዔውን የሚያካሄደው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት በኢትዮጵያ ስላለው የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ውሳኔዎች እንዲያስተላልፍ አለም አቀፍ የሰብዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ጥያቄን በድጋሚ አቀረቡ።
ሂማን ራይትስ ዎች፣ ፍሪደም ሃውስ ኢንተርናሽናል፣ ፌዴሬሽን ፎር ሂማን ራይትስ የተሰኙና ሌሎች ተቋማት ምክር ቤቱ በዚህ ጉዳይ ላይ ጠንካራ ውሳኔ እንዲተላለፍ ጠይቀዋል።
ከቀጣዩ ሳምንት ማክሰኞ ጀምሮ ለ15 ቀናት ጉባዔውን የሚያካሄደው ምክር ቤቱ በአለም ዙሪያ ስላሉ የሰብዓዊ መብት አያያዞችና ረገጣዎች ሰፊ ውይይት የሚያካሄድ ሲሆን፣ ውሳኔዎችን ያስተላልፋል ተብሎ ይጠበቃል። በዚሁ አመታዊ ጉባዔ የኢትዮጵያ ወቅታዊ የሰብዓዊ መብት ሁኔታ አጀንዳ ሆኖ እንዲቀርብና ውይይት እንዲካሄድበት ዳግም ጥያቄ መቅረቡን ሂውማን ራይትስ ዎች አርብ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
የጋራ ጥያቄ ያቀረቡት ከ10 የሚበልጡት ድርጅቶች፣ የኢትዮጵያ መንግስት ከአንድ አመት በፊት በኦሮሚያ ክልል የተፈጸመው ግድያና እስራት በገለልተኛ አካል ምርመራ እንዲካሄድበት ፈቃደኛ እንዲሆን፣ ጫና መደረግ እንዳለበት በደብዳቤያቸው አሳስበዋል።
ኢትዮጵያን በአባልነት የያዘው ይኸው ምክር ቤት በየአመቱ ልዩ ጉባዔን በማካሄድ የአለም የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ላይ ግምገማን እንደሚያካሄድ ለመረዳት ተችሏል።
የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ምክር ቤት ምርመራን ለማካሄድ ጥያቄ አቅርቦ በመንግስት የተከለከለ ሲሆን፣ በቅርቡ በሃገሪቱ ጉብኝትን አድርገው የነበሩት ሃላፊው ዘይድ ራድ አልሁሴን ጥያቄያቸውን በድጋሚ ማቅረባቸው ይታወሳል።
መንግስት እስካሁን ድረስ ለጥያቄው የሰጡት ምላሽ ባይኖርም ሂማን ራይትስ ዎች፣ ፍሪደም ሃውስ ኢንተርናሽናል፣ ፌዴሬሽን ፎር ሂማን ራይትስ የተሰኙና ሌሎች ተቋማት ምክር ቤቱ በዚህ ጉዳይ ላይ ጠንካራ ዕርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል።
ለእስር ተዳርገው የሚገኙ ጋዜጠኞች የፖለቲካ እስረኞች እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ግለሰቦች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፈታት እንዳለባቸው ድርጅቶቹ በጋራ ባቀረቡት የውሳኔ ደብዳቤ አብራርተዋል።
ከአንድ አመት በፊት በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ከ24ሺ የሚበልጡ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸው ይታወሳል። ይሁንና አብዛኞቹ ሰዎች ከወራት እስራት በኋላ የተለቀቁ ሲሆን፣ ወደ አምስት ሺ የሚጠጉ ደግሞ ክስ ይመሰርትባቸዋል ተብሏል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተግባራዊነት የሚከታተለው ኮማንድ ፖስት ታሳሪዎቹ ክስ እንደሚመሰርትባቸው ለፓርላማ ቢገልጽም፣ ክሱ መቼ እንደሚመሰረት የሰጠው ዝርዝር መረጃ የለም።
አሜሪካንን ጨምሮ የአውሮፓ ህብረትና የተለያዩ አካላት ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለሰብዓዊ መብት ረገጣ ምክንያት ይሆናል ሲሉ ስጋታቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል።