ግንቦት ፳፭ ( ሃያ አምስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የግንቦት 20 በአልን ምክንያት በማድረግ ለመከላከያ አባላት ገለጻ በተደረገበት ወቅት የጦር መኮንኖች ያቀረቡዋቸው ጥያቄዎችና የሰነዘሩዋቸው አስተያየቶች ከዚህ በፊት ያልተለመዱና ያልታዩ በመሆኑ፣ ወታደራዊ አዛዦችን አሳስቧል። በቅርቡም በመካለከያ ውስጥ አዲስ ጥልቅ ተሃድሶ ሊጠራ እንደሚችል ምንጮች ተናግረዋል። በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለሚገኙ የመከላከያ መኮንኖች ግንቦት20ን በማስመልከት አገሪቱ ስለምትገኝበት ወቅታዊ ሁኔታ ገለጻ ተደርጎላቸው ነበር። ነገር ግን ባዛዦች የቀረበውን ጽጌረዳ የሆነ ሪፖርት የተቀበለው አዛዥ አልነበረም ሲሉ ምንጮች ገልጸዋል።
በጣም ወሳኝ የሚባሉ የብሄር ብሄረሰብ መብቶች፣ አገሪቱ አንድነት፣ የሙስና ፣ የመልካም አስተዳደርና የመከላከያ ሚናን በተመለከተ ጥያቄዎች ቀርበዋል።
አብዛኞቹ የህወሃት ታጋዮች በብሄራዊ መግባባት ዙሪያ ትኩረት አድርገው ጥያቄዎችን ሲያቀርቡ፣ ከአማራ ክልል ተፈናቀሉ የተባሉ የትግራይ ተወላጆችን በምሳሌነት በማንሳት ነው። የህወሃት መኮንኖች ስጋታቸውን በግልጽ ሲናገሩ፣ የሌሎች አካባቢ ተወላጆች ደግሞ በብዛት ስለ ሙስና፣ የመልካም አስተዳደር ችግርና በአገሪቱ ተፈጥሮ ስለነበረው ተቃውሞ ጥያቄዎችን አቅርበዋል።
ስብሰባዎችን የመሩት ካድሬዎች በአንዳንድ ጥያቄዎች መደናገጥ እንደታየባቸውና ለመመለስም ተቸግረው እንደነበር ምንጮች ገልጸዋል። ኢሳት ባለፈው ሳምንት ብሄራዊ መግባባትን በተመለከተ ወታደሮች ካቀረቡዋቸው ጥያቄዎች መካከል አንዳንዶችን ድምጾች ማቅረቡ ይታወቃል። በአወያዮች እንደትልቅ ድል ይቀርብ የነበረውን የኢኮኖሚ እድገት ጥያቄ ውስጥ የከተቱ መኮንኖችም ነበሩ። ሻምበል ሁሴን የተባሉ የምእራብ እዝ አባል፣ ምንም እንኳ እድገት እና ለውጥ አለ ተብሎ ቢነገረንም፣ እድገቱና ለውጡ ግን በዳዴ እየሄደ ነው ሲሉ ተችተዋል። መኮንኑ በአሁኑ ሰአት ኪራይ ሰብሳቢነት አስከፊ ደረጃ ላይ ደርሷል ብለዋል።
ከቀበሌ ጀምሮ ባለው ተዋረድ ከፍተኛ ሙስና እንደሚፈጸም የገለጹት መኮንኑ፣ በሄዱባቸው ወረዳዎችና ቀበሌዎች ስራዎች የሚሰሩት በብላኔ ነው ብለዋል። ህዝቡ የሚናገረውና አመራሩ የሚናገረው እንደሚለያይ የሚገልጹት መኮንኑ፣ ድርጅቱ አሁን የያዘው መስመር እንዲቀጥል ከተፈለገ ከታች ያለው ሁኔታ መቀየር አለበት ብለዋል።
ሌላው አስተያየት ሰጪ የሆኑት መቶ አለቃ ሲሳይ ደግሞ፣ ባህርዳር ከተማ ውስጥ ያጋጠማቸውን የመልካም አስተዳደር ችግር ገልጸዋል። ሃቢታት በተባለው ድርጅት ህዝቡ የጉልበት ስራ እየሰራ ገንዘብ ሲያጠራቅም ቢቆይም አሁን ግን ገንዘብ የለም መባላቸውን ገልጸዋል።
በቅርቡ በአገሪቱ የተፈጠረው የለውጥ እንቅስቃሴ የጦር መኮንኖች የአገሪቱን ጉዳይ ከድርጅት ቅስቀሳ በዘለለ እንዲመለከቱት እንዳደረጋቸው ምንጮች ያምናሉ። የግንቦት20ን በአል ሰበብ በማድረግ በመከላከያ ውስጥ የተደረጉት ስብሰባዎች የመከላከያ መኮንኖች የያዙትን አቋም ለማወቅ ተብለው የተዘጋጁ መሆናቸውን የሚናገሩት እነዚህ ምንጮች፣ የስብሰባው ውጤት ዳግም ተሃድሶ እንደሚያስጠራና የማጥራት ዘመቻ ሊካሄድ እንደሚችል እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።