ኢሳት (ግንቦት 24 ፥ 2009)
የኮሎኔል አስናቀ እንግዳ የቀብር ስነስርዓት በዩኤስ አሜሪካ ዋሽንግተን ተፈጸመ። በ5 አመታቱ የአርበኝነት ተጋድሎ ተሳታፊው የነበሩትና ሃገራቸው በውትድርና ውጊያ ያገለገሉት ኮሎኔል አስናቀ እንግዳ በ 103 አመታቸው ያረፉት ግንቦት 21, 2009 አም ነበር።
ከአባታቸው ከአቶ እንግዳ ገ/ማሪያም እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ውቤቴ ገ/ስላሴ በጎንደር ክፍለ ሃገር ደብረታቦር አውራጃ አየር ማሪያም ደብር ጥር 7 ቀን 1906 አም የተወለዱት ኮሎኔል አስናቀ እንግዳ፣ በ5 አመታቱ የአርበኝነት ተጋድሎ ከደጃዝማች አያሌው ብሩ ሰራዊት ጋር ለሃገራቸው ነጻነት መታገላቸውን የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል።
ከነጻነት በኋላ በቀዳማዊ ሃይለስላሴ ጦር ት/ቤት በመግባት በ1938 በመኮነንት የተመረቁት ኮ/ል አስናቀ እንግዳ፣ የምስራቁ ሰራዊት አንበሳው 3ኛ ክፍለ ጦር ባልደርባ ሆነው በቀዳማዊ ሃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ከሶማሊያ ጋር በተደረገው ጦርነት ተሳታፊ በመሆን ሃገራቸውን መታደጋቸውም ተመልክቷል።
በንጉሰ ነገስቱ ላይ አሲረዋል በሚል ከነፊታውራሪ ሃይሉ ክብረት ጋር የታሰሩት ኮ/ል አስናቀ እኝግዳ፣ በ1953ቱ የጄኔራል መንግስቱ ንዋይ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተሳታፊ በመሆናቸው ለ5 አመታት በወህኔ ቆይተዋል።
ስለኮሎኔል አስናቀ እንግዳ አቶ ማለዳ ዘውዱ ምስክርነት ሰጥተዋል።
የንጉሱ ስርዓት ከተወገደ በኋላ በደርግ መንግስት ላይ በማመጽ ከነፊታውራሪ አየለ ጓዴ ጋር በመሆን፣ ከኢህአፓም ጋር በኋላም ከኢዲዩ ጋር መታገላቸውንም በቀብራቸው ስነስርዓት ከተነበበው የህይወት ታሪካቸው መረዳት ተችሏል። የኢትዮጵያ ህዝብ አብዮታዊ ፓርቲ፣ ኢህአፓም በቀድሞ በትግል ጓዱ ህልፈት የተሰማውን ሃዘን ባወጣው መግለጫ ገልጿል።
“ሸክም የማይከብደው ህዝብ” የሚለውን ጨምሮ ዘጠኝ ያህል መጽሃፍት የጻፉትና ሃገራችውን በውትድርና ሙያ ያገለገሉት የኮ/ል አስናቀ እንግዳ ጸሎተ-ፍትሃት በደብረሃይል ቅዱስ ገብርዔል ቤተክርስቲያን ከተካሄደ በኋላ ግንቦት 24 ፥ 2009 እኤአ ጁን 1 ፥ 2007 በዋሽንግተን ዲሲ ፎርትሊንክ መካነ መቃብር ተፈጽሟል።