ግንቦት ፳፫ ( ሃያ ሦስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኢህአዴግ አባላት ለኢሳት የአዲስ አበባ ዘጋቢ እንደገለጹት፣ ኢህአዴግን በመሰረቱት አራት ድርጅቶች መካከል ያለው መናበብ፣ ከዚህ ቀደም ባልታየ መልኩ በመዳከሙ፣ አቅጣጫ ሰጥቶ የሚመራ አካል እየጠፋ ነው።
በኢህአዴግ ታሪክ የአባላቱ መንፈስ በዚህ ደረጃ የወደቀበትን ጊዜ አናስታውስም የሚሉት አባሎቹ፣ ማእከላዊነት የሚባል ነገር በመጥፋቱ ሁሉም በራሱ የመሰለውን ውሳኔ እየሰጠ ነው ይላሉ።
“አለመግባባቱ፣ ጥርጣሬውና ራስን ማእከል አድርጎ ውሳኔ የመስጠቱ አካሄድ እየተስፋፋ በመምጣቱ፣ እንደ ድርጅት መናበብ” መጥፋቱን የሚገልጹት አባላቱ፣ ብዙዎቹ ተስፋ እየቆረጡ መልቀቂያ እያስገቡ ነው ይላሉ። ህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ የመልቀቂያ ጥያቄ የሚያቀርቡ አባሎች መበራከታቸው፣ በድርጅቱ ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሮበታል።
በህወሃት እና በብአዴን፣ በህወሃት እና በኦፒዲዮ ደጋፊዎች መካከል ያለው አለመግባባት የኢህአዴግን ህልውና እንደተፈታተነው የሚገልጹት አባላቱ፣ የድርጅቱ ነባር አመራሮች በየቦታው እየዞሩ ሁኔታውን ለመቀየር የሚያደርጉት ጥረት አልተሳካለቸውም ይላሉ።
በፓርቲው ውስጥ ያለው የአባላቱ የእርስ በርስ ጥላቻ የድርጅቱን ህልውና ጎድቶታል ሲሉ በአንድ የአባላት ስብሰባ ላይ የተናገሩት አቶ በረከት፣ ወጣት ተተኪ አመራሮች በጥላቻ ወሬዎች እንዳይወናበዱ መክረዋል። ይሁን እንጅ ከተሰብሳቢዎች መካከል የህወሃትን ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ የበላይነት አንስተው ለሞገቱ አባላቱ አቶ በረከት መልስ መስጠት ሳይችሉ ቀርተዋል።
የኢህአዴግ አባላት የእርስ በርስ ጥላቻ ወደ ህዝቡ ወርዷል በማለት የተናገሩት አቶ በረከት፣ በከፊልም የራሳቸውን አባላት ተጠያቂ አድርገዋል። የእኛን አባላትና ተቃዋሚዎች መለየት አልተቻላም፤ የእኛ አባላትም፣ ተቃዋሚዎችም የሚያነሱትና የሚጥሉት አጀንዳ አንድ ነው፤ ይህን አመለካከት መለወጥና ከላያችን ላይ የተለጠጠፈውን ጥላቻ አራግፈን መሄድ አለብን፣ ያ ካልሆነ ግን በድርጅቱ ውስጥ ታቅፎ መቀጠል አይቻልም ሲሉ ምክር አዘል ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።
የድርጅቱ አባላት በመላ አገሪቱ በነበረው ተቃውሞ የሞራል ስብራት እንደደረሰባቸው አንዳንድ አባላት ሲናገሩ፣ “ከሁሉም በላይ የኢኮኖሚ እድገት በመጣበት፣ አባይን የሚያክል ፕሮጀክት ነድፈን በምንቀሳቀስበት ወቅት፣ ህዝቡ እንዴት ሊደግፈን አልቻለም፤ ያዳነን መከላከያ እንጅ ስራችን አይደለም፤ በዚህ ሁኔታስ እንዴት መቀጠል ይቻላል” ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል።
ህዝቡ የተቃዋሚዎችን ወሬ መስማቱ ተፈጥሯዊ እንደሆነ፣ ኢህአዴግ ለረጅም ጊዜ በስልጣን ላይ መቆየቱ በአባላቱም ሆነ በአመራሩ ዘንድ መሰላቸት እንደተፈጠረ፣ ከሁሉም በላይ ኪራይ ሰብሳቢነት በመስፋፋቱ ህዝቡ ኢህአዴግን ሊቃወም እንደቻለ የስብሰባው መሪዎች ገልጸዋል።
አህአዴግ በድርጅቶች መካከል ያለውን የእርስ በርስ ጥላቻ በምን መልኩ እንደሚፈታው ስትራቴጂ አለመቀየሱን ከስብሰባው ለመረዳት መቻላቸውን አባላቱ ለዘጋቢያችን ተናግረዋል።