ግንቦት ፳፫ ( ሃያ ሦስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ረቡዕ ለሚጀመረው ፈተና ከማክሰኞ ጀምሮ የኢንተርኔት አገልግሎት መቁዋረጡ በማህበራዊ ድረገጾች ተጠቃሚዎች ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ፈጥሯል። ቁጥራቸው 1.2 ሚሊዮን የሚሆኑ የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች ብሄራዊ ፈተናውን የሚወስዱ ሲሆን በተጨማሪም 288 ሽህ የ12ኛ ክፍል የዩንቨርሲቲ መሰናዶ ብሄራዊ ፈተናውን በቀጣይ ሳምንት እንደሚወስዱ ሪፖርቶች አመላክተዋል።
የኢንተርኔት አገልግሎት ለ12 ሰዓታት ዝግ ሆነው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል። ከትናንት ከሰዓት ጀምሮ የመስመሮች መቆራረጥ ሁሉም ነገር ዝግ ነው።
ኢትዮጵያ በኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ረገድ በዓለም ላይ እጅ ኋላቀር ከሚባሉት አገራት ተርታ ትመደባለች። ከዚህም በላይ የኢንተርኔት አገልግሎትን በማቋረጥ እና ስለላ በማድረግ ሕዝባዊ አመጾችን ለማፈኛ ታውላለች።
በኢትዮጵያ ኢንተርኔት ዝግ መሆኑን አስመልክቶ የድንበር የለሽ የኢንተርኔት ቡድን የአፍሪካ ዴስክ ሃላፊ የሆኑት ጁሊየ ኦዎኖ ት ”አላስፈላጊ የሆነ ውሳኔ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ የዲጂታል ኢንተርኔት ተጠቃሚነት መብቱን የሚጻረር ነውረኛ ድርጊት ነው” ሲሉ ኮንነዋል።
ከዚህ ቀደም አንዳንድ የኢንተርኔት አግልገሎቶች የነበሩ ቢሆንም፣ አሁን ግን ሁሉም አገልግሎቶች ሙሉ በሙሉ ተቋርጠዋል። የኢንተርኔት መቋረጡ በባንኮችና ሌሎች አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ ከፍተኛ ችግር ፈጥሯል።