ከ10ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ጋር በተያያዘ የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋረጠ

ኢሳት (ግንቦት 23 ፥ 2009)

በመላው ኢትዮጵያ ረቡዕ መሰጠት ከጀመረው የ10ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ጋር በተያያዘ በሃገሪቱ ከማክሰኞ ምሽት ጀምሮ የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋረጠ።

ብሄራዊ ፈተናው ተሰርቆ ሊሰራጭ እንደሚችል ስጋት መኖሩ ለአገልግሎቱ መቋረጥ ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ኳርትዝ አፍሪካ የተሰኘ መጽሄት የተለያዩ አካላትን ዋቢ በማድረግ ረቡዕ ዘግቧል። በመዲናይቱ አዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች በበኩላቸው ችግሩ ረቡዕ ድረስ የዘለቀ መሆኑን በመግለፅ ላይ መሆናቸውን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

ለ12 ሰዓታት ሙሉ ለሙሉ ተቋርጦ የነበረው የኢንተርኔት አገልግሎት ረቡዕ በከፊል መቀጠሉ ቢነገርም፣ ችግሩ በበርካታ አካባቢዎች ዕልባት አለማግኘቱን መጽሄቱ በዘገባው አስፍሯል።

የትምህርት ሚኒስቴርም ሆነ ሌሎች የመንግስት ባለስልጣናት በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያን ያልሰጡ ሲሆን፣ የ10ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተናው ከግንቦት 23 እስከ ሰኔ 1 ፥ 2009 አም እንደሚቆይ ታውቋል።

ባለፈው አመት ተመሳሳይ የብሄራዊ ፈተና ለመስጠት በዝግጅት ላይ እንዳለ የብሄራዊ ፈተናው በማህበራዊ ድረገጾች ተሰራጭቶ እንደነበር ይታወሳል።

የብሄራዊ ፈተናው መሰረቅን ተከትሎም የትምህርት ሚኒስቴር ፈተናው በድጋሚ እንዲሰጥ አድርጎ የጊዜ ሰሌዳው ተራዝሞ እንደነበር አይዘነጋም።

ይሁንና ማክሰኞ ምሽት አገልግሎቱ የተቋረጠው የኢንተርኔት አገልግሎት ከፈተናው መሰጠት ጋር ግንኙነት ይኑረው አይኑረው ጉዳዩ የሚመለከተው የመንግስት አካል ምላሽን አልሰጠም።

በአለም አቀፍ ደረጃ መጠነኛ የኢንተርኔት አገልግሎት ያላት ኢትዮጵያ በሃገር ውስጥ ተቃውሞዎች በሚነሱ ጊዜ አገልግሎቱን ስታቋርጥ መቆየቷን ካርትዝ አፍሪካ የተሰኘው መጽሄት በዘገባው አመልክቷል።

በኢንተርኔት አገልግሎት አጠቃቀምና መብት ዙሪያ የሚሰራው ኢንተርኔት ሳን ፍሮንቲየርስ የተሰኘ ተቋም በበኩሉ ማክሰኞ አገልግሎቱን ለማቋረጥ የተወሰደው ዕርምጃ አላስፈላጊና የኢትዮጵያውያንን መብት የሚጥስ ነው ሲል ምላሽን ሰጥቷል።

በተያዘው ወር በማህበራዊ ድረገጾች የተለያዩ ሃሳቦችና አስተያየቶችን የጻፉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራርና ጋዜጠኞች ከአመት በላይ የሚዘልቅ እስራት ተላልፎባቸው እንደነበር መጽሄቱ በዘገባው አውስቷል።

ረቡዕ የተጀመረው የ10ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ከተጠናቀቀ በኋላ የፊታችን ሰኞ የ12ኛ ክፍል ዩኒቨርስቲ መግቢያ ለአራት ተከታታይ ቀናት እንደሚሰጥ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።

ወደ 300 ሺ አካባቢ የሚጠጉ ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል የዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተናን እንደሚወስዱ ይጠበቃል።