ኢሳት (ግንቦት 23 ፥ 2009)
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአስተዳደር ስርዓት ነጻነት እንዲኖረው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚደንት ፕሮፌሰር አድማጹ ጸጋዬ ጥሪ አቀረቡ።
የመንግስት የፋይናንስ ህግ ማዕቀፎችም የተሰጠውን ተልዕኮ ለማስፋፋት እንቅፋት መሆናቸውን የዩኒቨርስቲው ፕሬዚደንት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መግለጻቸውን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ዩኒቨርስቲው በራሱ እቅድ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገራት በሚያከናውናቸው ፕሮግራሞች የሚሰበሰበው የውስጥ ገቢ ቢኖረውም የመንግስት የፋይናንስ ስርዓት ግን ዩኒቨርስቲው የሚያመነጨውን የውስጥ ገቢ እንዲጠቀም እንደማይፈቅድ ፕሬዚደንቱ የምክር ቤቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በዩኒቨርስቲው ጉብኝት ባካሄደ ጊዜ አስረድተዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከውጭ አገራት መምህራን በኮንትራት ሲያስመጣ ለተለያዩ ወጪዎች ክፍያን በዶላር ይፈጽማል ያሉት ፕሮፌሰር አድማጹ ጸጋዬ፣ ክፍያው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ያልተጠቀሰ በመሆኑ በኦዲት ሪፖርት ተጠያቂ እየሆነ መሆኑንም አስታውቀዋል።
በቅርቡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከመንግስት የፋይናንስ ህጎችና ደንቦች ውጭ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ አድርጓል መባሉ ይታወሳል።
ይሁንና የአዲስ አባባ ዩኒቨርስቲ የመንግስት የፋይናንስ ህግ ማዕቀፎች ለችግሩ ምክንያት መሆናቸውን ገልጸዋል።
ችግሮቹን ለመቅረፍም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአስተዳደር ስርዓት ነጻነት ሊኖረው ይገባል ሲሉ የዩኒቨርስቲው ፕሬዚደንት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በበኩሉ የዩኒቨርስቲው አመራሮች ያቀረቡትን ጥያቄዎች ጉዳዩ ለሚመለከተው አካል እንደሚያቀርብ ምላሽ ሰጥቷል። የዩኒቨርስቲው በርካታ መምህራት በተለያዩ ጊዜያት መንግስት በአስተዳደራዊ ጉዳዮች የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት በትምህርት ጥራቱ ላይ ተፅዕኖን አድርጓል በማለት ሲገልጹ ቆይተዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር እኛ ሌሎች የመንግስት ባለስልጣናት ችግሩ ዕልባት እንደሚያገኝ ቃል ቢገቡም፣ የታየ ለውጥ አለመኖሩን መምህራን ይገልጻሉ።