ኢሳት (ግንቦት 22 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ስልጣኑን የያዙት የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት መሪዎች የትግራይ ተወላጅ ያልሆነ ኢትዮጵያዊ በአለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ በሃላፊነት እንዲሰራ ድጋፍ እንደማያደርጉ አንድ ታዋቂ ኢትዮጵያዊ ገለጹ።
በአፍሪካ ልማት ባንክ እስከ ምክትል ፕሬዚደንትነት ለ15 አመታት ያገለገሉት አንጋፋው ኢትዮጵያዊ አቶ ተካልኝ ገዳሙ “Republican on the Throne” በተባለውና ከአመታት በፊት ለንባብ ባቀረቡት መጽሃፋቸው እንደገለጹት ለአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዚደንትነት ሳይወዳደሩ የቀሩት የኢትዮጵያ መንግስት የድጋፍ ወረቀት ስለነፈጋቸው መሆኑን አውስተዋል።
ይህ በእርሳቸው እንዳልተጀመረና ከርሳቸው በፊትም በሌሎች የትግራይ ተወላጆች ባልሆኑ ኢትዮጵያውያን ላይ ተፈጻሚ መሆኑንም በመጽሃፋቸው ያመለከቱ ሲሆን፣ ለኢሳት በሰጡት ቃለምልልስ ይህንኑ በዝርዝር ተመልክተዋል።
የዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን በአሜሪካ ኤሊኖይና በስመጥሩ ሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ ካጠናቀቁ በኋላ፣ በኒውዮርክ የተባበሩት መንግስታት ሰራተኛ በመሆን ስራ የጀመሩት አንጋፋው ኢትዮጵያዊ አቶ ተካልኝ ገዳሙ፣ ከቀዳማዊ ሃ/ስላሴ ዘመን በመጨረሻና በደርግ ዘመን በሚኒስትርነት ሃገራቸውን አገልግለዋል።
በፈቃዳቸው ስልጣናቸውን በመልቀቅ ወደ አቪዣን በአፍሪካ ልማት ባንክ እስከምክትል ፕሬዚደንትነት 15 አመታት ያልገለገሉት አቶ ተካልኝ ገዳሙ፣ በቦታው ባሳዩት ውጤታማነት ለፕሬዚደንትነት እንዲወዳደሩ ከተለያዩ ሃገራት አምባሳደሮች ግፊት ቢደረግም፣ በኢትዮጵያ መንግስት ድጋፍ ባለማግኘታቸው ሳይሳካ መቅረቱን ለኢሳት በሰጡት ቃለምልልስ አስታውሰዋል።
አቶ ተካልኝ ገዳሙ በመጽሃፋቸው እንዳመለከቱት የትግራይ ተወላጆች ያልሆኑ ኢትዮጵያውያን በአለም አቀፍ መድረክ ስፍራ እንዳያገኙ ድጋፍ መንፈግ የተጀመረው በርሳቸው እንዳልሆነና ሌሎች አብነቶችን ጠቅሰዋል።
አቶ ተፈራ ራስወርቅ የተባበሩት መንግስታት አካል ለሆነው ኢንተርናሽናል ቴሌኮሚኒኬንሽን ዩኒየን እንዳይወዳደሩ በመንግስት ድጋፍ መነፈጋቸውን አስታውሰው፣ አቶ ይልማ ታደሰም ለአፍሪካ ህብረት ያደርጉት የነበረውን ውድድርም በተመሳሳይ በመንግስት ለዜጎቹ በነፈገው ድጋፍ መስተጓጎሉም አመልክተዋል።
ስልጣን ላይ ያለው የኢትዮጵያ መንግስት የትግራይ ተወላጆችና የህወሃት አባል የሆኑት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ለአለም አቀፍ የጤና ድርጅት እንዲወዳደሩ ድጋፍ ከመስጠት ባሻገር የቅስቀሳ ስራ እንዲሰሩ ከ60 በሚበልጡ ሃገራት እንዲንቀሳቀሱ ሁኔታዎችን አመቻተዋል።
ምርጫው በተካሄደበት ጀኔቫም የመንግስት ልዑካንን የላከ ሲሆን፣ ዶ/ር ቴዎድሮስ አሸንፈው ወደ ሃገር ቤት ሲመለሱም የጀግና አቀባበል አድርጎላቸዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ የትግራይ ተወላጅ ወጣቶች በተዘጋጀው መድረክ ላይም ተገኝተው ደማቅ መስተንግዶ ተደርጎላቸዋል። የትግራይ ወጣቶችም የአቶ መለስና የዶ/ር ቴዎድሮስን አርዓያ እንዲከተሉ ገልጸዋል።
ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የአለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ሆነው መመረጣቸውን በተመለከተም በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የተባበሩት መንግስታት ዋና ዳይሬክተር ዋና ሃላፊነትን የያዙ ያህል እየተነገረ ይገኛል።
የዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ስልጣን ከተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሃፊነት ጋር በማነጻጸር እንዲመለከቱ ኢሳት ያነጋገራቸው በጄኔቭ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት ዶ/ር ካሳ ከበደ ልዩነቱን በአንድ ከተማ ከንቲባና በከተማው ውስጥ በሚኖር አንድ ሃኪም ቤት ሃላፊ አስመስለውታል።