ግንቦት ፳፪ ( ሃያ ሁለት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የሰብአዊ መብት ጉባኤ በ142ኛ ልዩ መግለጫው ላይ እንደጠቀሰው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ ከመስከረም 29 ቀን 2009 ዓም ጀምሮ ከ22 ሺ በላይ ሰዎች የታሰሩ ሲሆን፣ በተለያዩ እስር ቤቶች ውስጥ አሰቃቂ የሆኑ የቅጣት እርምጃዎች በእስረኞች ላይ እንደሚፈጸሙ ገልጿል።
ሰመጉ ወታደራዊ ካምፖች ኮሌጆችና ትምህርት ቤቶች እስርቤት ሆነው ማገልገላቸውን ገልጾ፣ በተለይ በወታደራዊ እስር ቤቶች ውስጥ በእስረኞች ላይ የሚደርሰው ሰቆቃ ከባድ መሆኑን አመለክቷል።
በጦላይ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ጣቢያ ባዶ እግር ግርፋት፣ ጆሮን በእጅ አስይዞ ማኮብኮብና ምግብ መከልከል፣ እስረኞች እግራቸው ወደ ላይ ተሰቅሎ ወይም መሬት ላይ በደረታቸው ተኝተው እየተደበደቡ የስቃይ ምርምራ ይደረግባቸው እንደነበር እስረኞች እንደገለጹለት ጠቅሷል።
በተለይ በአዲስ አበባ፣ በጦላይና አዋሽ አርባ አካባቢ ታሰሪዎችን በሚያዋርድ እና ሰብአዊነት በጎደለው ሁኔታ በመጸዳጃ ሰአትም 114 ሰው በአንድ ላይ ወጥቶ ሜዳ ላይ ወይም በአንድ ጉድጓድ እንዲጸዳዱ መገደዳቸውን ድርጅቱ ገልጿል።
በጦላይ ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ በአንድ ጠባብ ክፍል ውስጥ 115 ሴቶች እንዲታሰሩ ተደርገው ስቃይ እንደተፈጸመባቸው፣ በአዋሽ አርባም በአንድ መኝታ ክፍል ውስጥ 114 እስረኞች ታሽገው እንዲቀመጡ መደረጉን እስረኞቹ ለሰመጉ ተናግረዋል።
በደብረታቦር እስር ቤት ውስጥ ከፍተኛ የውሃ ችግር በመኖሩ እስረኞቹ ለመጠጥም ሆነ ለመታጠቢያ ውሃ ማግኘት እንደማይችሉ፣ በሳምንት አንድ ቀን ብቻ የተወሰነ ውሃ እንደሚሰጣቸው፣ በዚህም የተነሳ ለውሃ ወለድ በሽታ እንደተጋለጡ አትቷል።
በፍኖተሰላም ደግሞ በማረሚያ ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ የአሳማ መንከሪያ የሚባል ማሰቃያ ቦታ መኖሩን አጋልጧል። የአስማ መንከሪያ የሚባለው የማረሚያ ቤቱ የሽንት ማጠራቀሚያ ሲሆን፣ ፖሊሶች አንዳንድ እስረኞችን እየወሰዱ ሽንት ውስጥ እየዘፈዘፉ እንደሚያሰቃዩ እና እንደሚደበድቡ ገልጿል።
ሰመጉ ኮሌጆችና ትምህርት ቤቶች ለማሰሪያ ቦታነት መዋላቸውን በምርምራ ሪፖርቱ ላይ አመልክቷል። ጥቅምት ላይ በኮንሶ ከዞን ጥያቄ ጋር በተያያዘ 37 ሰዎች በኮንሶ እንድሱትሪያል ዞን፣ 574 ሰዎች በኮንሶ ፖሊስ ኮሌጅ እንዲሁም 440 ሰዎች በኮንሶ ቴክኒክ እና ሙያ ትምህርት ቤት ታስረው እንደነበር እንዲሁም ህዳር ላይ በአላጌ ግብርና ኮሌጅ ፣ 75 ሰዎች፣ መስከረም ላይ በዲላ መምህራን ኮሌጅ 2600 ሰዎች፣ ጥቅምት ላኢ በአላጌ ግብርና ኬሎች እንደገና 33 ሰዎች ተስረው እንደነበር ጠቅሷል።
በፖለቲካ ፓርቲዎች ደረጃ 15 የሰማያዊ ፓርቲ አባላትና አመራሮች፣ 102 የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አባላትና አመራሮች እንዲሁም ከመኢአድ 11 አባላትና አመራሮች መታሰራቸውን ሰመጉ በሪፖርቱ አመልክቷል። ከደብረታቦር ዩኒቨርስቲ 15 ፣ ከጅማ ዩኒቨርስቲ 3 ተማሪዎች ሲታሰሩ፣ በምስራቅና ምእራብ ጎጃም ከመምህራን ደሞዝ ጭማሪ ጋር በተያያዘ 30 መምህራን ታስረው እንደነበር በሪፖርቱ አመልክቷል።
በሰመጉ ልዩ መግለጫ ላይ ከቀረቡት በርካታ የመብት ጥሰቶች መካከል በአቶ ካምቢሮ አይላቴ ጉዳኖ ላይ የደረሰውን ይገኝበታል። ከኮንሶ ህዝብ የዞን ጥያቄ ጋር በተያያዘ የመንግስት የጤና ተቋማት በመዘጋታቸው የእርሳቸው የግል ንብረት በሆኑት ፋሮ መካከለኛ ክሊኒክና የመድሃኒት መደብር ለህዝቡ አግልግሎት ሲሰጡ ቆይተዋል። ህዳር 04 ቀን 2009 ዓም የክልሉ ልዩ ሃይልና የፌደራል ፖሊስ አባላት ከደህንነቶች ጋር በመሆን ወደ ክሊኒካቸው በመሄድ ለታካሚዎች አገልግሎት መስጠት እንዲያቋርጡ ጠይቀዋል። በዚያው እለት ወደ ክሊኒክ በድጋሜ በመሄድ ስራ ሲጀምሩ “ክሊኒኩን ዝጉ፣ ሁዋላ ላይ እንነጋገራለን” የሚል የቃል ትእዛዝ ተሰጥቷቸዋል። ድርጀቱ ስራ እንዳይጀመር በመደረጉ ከ200 ሺ ብር በላይ የሚሆን ንበረት እየተባለሸ ነው። ግለሰቡ በተደጋጋሚ አቤቱታ ቢያቀርቡም ከኮማንድ ፖስቱ ጋር እየተነጋገርንበት ነው የሚል ምላሽ ከማግኘት ውጭ መፍትሄ አላገኙም ሲል ሰመጉ ጠቅሷል።
በጥቅምት ወር 2009 ኣም በኮንሶ ወረዳ ወፍጮ ቤቶች በመንግስት ታጣቂዎች እንዲዘጉ በመደረጋቸው ምክንያት ወደ ሌላ አካባቢ በመሄድ ለቀለብ የሚሆን እህል አስፈጭተው ይመለሱ የነበሩ ዜጎች የያዙትን የተፈጨ እህል የደቡብ ክልል ልዩ ሃይል አባላትና የመከላከያ ሰራዊት አባላት ደፍተውባቸዋል፤ ወደ መኖሪያ ቤቶች በመግባትም የበሰለ ምግብ ውስጥ አመድ ጨምረዋል፤ የመመገቢያ ቁሳቁሶችንም ሰባብረዋል ሲሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ለሰመጉ ገልጸዋል።
በዶ/ር አዲሱ ገብረእግዚአብሄር የሚመራው የመንግስቱ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በኮማንድ ፖስቱ (ወታደራዊ እዙ) የታሰሩት እስረኞች የእስር ቤት አያያዛቸው ጥሩ እንደነበር ሪፖርት ማውጣቱ ይታወቃል።