አርበኞች ግንቦት7 በአንድ የደህንነት አባል ላይ ጥቃት መፈጸሙን አስታወቀ

ግንቦት ፳፪ ( ሃያ ሁለት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ንቅናቄው ለኢሳት በላከው መግለጫ በደንቢያ ወረዳ ቆላድባ ከተማ ልዩ ስሙ ጎርጎራ ክፍል እየተባለ በሚጠራው ስፍራ ግንቦት21 ቀን 2009 ዓም ከምሽቱ አራት ሰዓት ላይ በአንድ የህወሃት የደህንነት አባል ላይ ጥቃት መፈጸሙን ገልጿል።
በደንቢያ ወረዳ የህወሃት ሰላይ በመሆን በአካባቢው ህዝብ ላይ ለሚደርሰው ግድያ ፣ አፈናና እስር ዋና ተጠያቂ ነው ባለው አብርሃ ተበጀ መኖሪያ ቤት እና ድርጅት ላይ ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል።ጥቃቱ ለህወሃት በመሰለል በህዝቡ ላይ ግፍ እንዲደርስ ለሚያደርጉት ማስተማሪያ ይሆን ዘንድ የተፈጸመ ነው ሲል የጥቃቱን ምክንያት አስቀምጧል።
በተመሳሳይ ዜናም ግንቦት19 ቀን 2009 ዓም ምሽት 6 ሰአት ላይ በዚሁ ወረዳ ከንች ውሃ በተባለው ቦታ ላይ አንድ የህወሃት አባል ንብረት የሆነ የሩሎ ማሽን ጥቃት ተፈጽሞበት መቃጠሉን ገልጿል።
ጥቃቱ የተፈጸመው በህዝቡ ጥቆማ መሆኑን የገለጸው ድርጅቱ፣ ጥቃቱን በፈጸሙት ታጋዮች ላይ ምንም ጉዳት አለመድረሱን ተናግሯል። አርበኞች ግንቦት7 ወሰድኩት ባለው እርምጃ ላይ ገዢው ፓርቲ መግለጫ አልሰጠም።
በዚህ ወረዳ ሰሞኑን የመከላከያ ሰራዊት አባላት የጦር መሳሪያቸውን ሽጠው በመጥፋታቸው ከፍተኛ ፍተሻ እየተካሄደ መሆኑን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
ምን ያክል ወታደሮች እንደጠፉ ለማወቅ ባይቻልም፣ ወታደሮች ህዝቡ የጠፉ ወታደሮች ያሉበትን ቦታ እንዲጠቁሙ ሲያስፈራሩ ሰንብተዋል። ወታደሮች የጠፉት ባለፈው ቅዳሜ ነው።