የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ በሁዋላ በርካታ ዜጎች መገደላቸው ሰመጉ አስታወቀ

ግንቦት ፳፩ ( ሃያ አንድ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የቀድሞው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ጉባኤ የአሁኑ ሰብአዊ መብት ጉባኤ (ሰመጉ) ባወጣው 142ኛ ልዩ መግለጫ፣የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ ከመስከረም28 ቀን 2009 ዓም ጀምሮ ከህግ አግባብ ውጭ በርካታ ዜጎች ተገድለዋል፣ ቆስለዋል፣ ተደብድበዋል፣ በመደበኛ እስር ቤቶችና ከመደበና እስር ቤቶች ውጭ በርካታ ሰዎች ለእስር ተዳርገዋል፣ የደረሱበትም የማይታወቁ በርካታ ናቸው ብሎአል።
ሰመጉ ከህግ አግባብ ውጭ ተገደሉ ያላቸውን ቢያንስ የ19 ሰዎችን ዝም ዝርዝር በፎቶ አስደግፎ አውጥቷል።

በምዕራብ ወለጋ ዞን በላሎ ወንጅ ላሎ አሳቢ ወረዳ ነዋሪ የሆነው የ29 ዓመቱ አርሶአደር ደገፉ ሽፈራው ከቤቱ ሲወጣ በመከላከያ ሰራዊት አባላት በጥይት ቀኝ ጎኑ ላይ ተመትቶ ከወደቀ በሁዋላ፣ ቤተሰቦቹ ጊምቢ ሆስፒታል ቢወስዱትም መስከረም 29 ቀን 2009 ዓም ህይወቱ አልፏል። ግድያው የተፈጸመው ቀደም ብሎ በላሎ ወንጅ የኢሬቻን ቀውስ ተከትሎ ከተካሄደና ከዚያም በፊት ከነበሩት የተቃውሞ ሰልፎች ጋር በተያያዘ መሆኑን ምስክሮች ለሰመጉ ገልጸዋል።
የ28 ኣምት ወጣት የሆነው በሰዬ ወረዳ በሳማድ ቀበሌ ነዋሪ የሆነው የመከላከያ ሰራዊት አባል የነበረው መገርሳ በድሉ መስከረም 28 ቀን 2009 ዓም በጥይት ተገድሏል።

በምዕራብ ወለጋ ነዋሪ የሆነው የ33 ዓመቱ ጌቱ ታምሩ በመከላከያ ሰራዊት አባላት መስከረም 28 ቀን 2009 ዓም ተገድሏል። የ19 ዓመቱ ኢፋ ደንጋታም ደምቢ ዶሎ ከተማ ታቦር ቀበሌ ላይ ጥቅምት 02 ቀን 2009 ዓም ከምሽቱ አንድ ሰአት ላይ ከጓደኞቹ ጋር በመንገድ ላይ እየሄደ እያለ በመከላከያ ሰራዊት አባላት በጥይት ተደብድቦ ህይወቱ አልፏል።
የ30 ዓመቱ ለታ ሊካሳ ደምቢዶሎ፣ የ26 አመቱ ኮኒሳ ሊካሳ ደምቢዶሎ፣ የ30 አመቱ ኢብሳ ቢኬታ ምስራቅ ወለጋ አርጆ ጉደቱ ከተማ ፣ የ18 አመቱ ተማሪ ደረጀ ተስፋየ፣ ደምቢዶሎ ወረዳ፣ የ28 አመቱ ደሳለኝ ጋሪ፣ ቦጂ ወረዳ፣ ወንድማማች የ25 አመቱ ማረጉ ጀማሎ ፣ የ18 ዓመቱ አብዲሳ ጀማሎ እንዲሁም ቶላ ጀማሎ አርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ ላይ መስከረም 30 ቀን 2009 ዓም ወታደሮች ወደ ቤታቸው ሰብረው በመግባት በጥይት ደብድበው ገድለዋቸዋል።
በማግስቱ ደግሞ የ23 አመቱ መሃመድ በያኖ በወታደሮች የተገደለ ሲሆን፣ ሁለቱ ወንድማማቾች በአንድ ጉድጓድ፣ መሃመድና አንደኛው ወንድማቸው በሌላ ጉድጓድ ተቀብረዋል።

ሟች ቦጃ በቀለ ምስራቅ ወለጋ ፣ ዲጋ ወረዳ፣ ገመቺሳ ቀበሌ ከአጎቶቹ ጋር እየተማረ እያለ ትምህርት ቤት ለ2 ሳምንታት በመዘጋቱ የፋሲካን በአል ከቤተሰቦቹ ጋር ለማሳለፍ ወደ ወረ አካባቢ ሄደ። ሚያዚያ 5 ቀን 2009 ዓም ማምሻውን ከጓደኞቹ ጋር ለማደር እራት በልቶ ወጣ። ከሌሊቱ 7 ሰአት ላይ ተገደለ።
የአክስቱ ልጅ ፖሊስ ጣቢያ ሄዳ ስትጠይቅ ፖሊሶች ፎቶውን አሳዩዋት። እርሷም ወንድሟ መሆኑን ገልጻላቸው፣ ቤት ደርሳ ለቤተሰቦች እስከምትነገር ድረስ ፖሊሶች አስከሬኑን በቀን ሰራተኞች አማካኝነት ሚያዚያ 6 ቀን 2009 ዓም በጂካ መካነእየሱስ ቤተክርስቲያን፣ ጥልቀቱ ከአንድ ሜትር በማይበልጥ ጉድጓድ ውስጥ በሸራ ጠቅልለው እንዲቀበር አድርገዋል። በሁዋላም በፖሊስ የተቀበረውን አስከሬን በማውጣት ሚያዚያ 7 ቀን 2009 ዓም ወላጆቹና ዘመዶቹ በተገኙበት በሙሉ ወንጌል ቤተክርስቲያን የቀብር ስነስርዓቱ ተፈጽሟል።
መ/ር ካሳታ ኞኬ የ32 አመት ጎልማሳ ሲሆን የ3 ልጆች አባትም ነው። ታህሳስ 05 ቀን 2009 ዓም ኮንሶ ወረዳ ዶክቱ አካባቢ ከምሽቱ 12 ሰአት ላይ ዩኒፎርም የለበሰ የመከላከያ ሰራዊት አባል ሟች መምህር ካሳታንና ሌሎች ሁለት ሰዎችን ሲያባርሩዋቸው፣ መ/ር ካሳታ ተደናቅፎ መውደቁን ፣ ከወደቀበት ለመነሳት ሲሞክር በተተኮሰበት ጥይት ጭንቅላቱ ላይ ተመትቶ መገደሉን በስፍራው የነበሩ የአይን ምስክሮች ለሰመጉ ገልጸዋል። መምህሩ 3 ልጆቹን እንዲሁም በእድሜ የገፉ አባቱንም እየረዳ ያስተዳደር ነበር።

በኮንሶ ወረዳ ዋና ሳጅን ገመዳ ሮባ የፖሊስ ሰራዊት አባል የነበረ ሲሆን፣ በኮንሶ ህዝብ የዞን ይገባኛል ጥያቄ ጋር በተያያዘ ሰራተኞች ስራ በማቆማቸውና የሁሉም የመንግስት ሰራተኞች ደሞዝ በመቋረጡ ምክንያት ( የፖሊሶች ጨምሮ) ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር ሲሉ የፖሊስ ስራቸውን ትተው በግብርና መተዳደር ጀምረው ነበር። ዋና ሳጅን ገመዳ ሮባ ጥቅምት 12 ቀን 2009 ዓም ከረፋዱ 4 ሰአት አካባቢ በሰገን ጨረቅሌ አካባቢ በእርሻ ስራ ላይ እያሉ በታጠቀ የፖሊስ አባል ኩላሊታቸው ላይ በጥይት ተመተው ተገድለዋል። የ49 ዓመቱ ዋና ሳጅን ገመዳ ባለትዳርና የ10 ልጆች አባት ነበር።

የ64 ዓመቱ አቶ ምክሩ ቸኮል ደግሞ በምዕራብ ጎጃም ዞን ባህርዳር ዙሪያ ወረዳ ጢስ አባይ ቀበሌ 01 በግብርና ስራ የሚተዳደሩ፣ ባለትዳርና የ6 ልጆች አባት ነበሩ። ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ተባብረሃል በሚል ምክንያት ጥቅምት 22 ቀን 2009 ኣም ከቀኑ 6 ሰአት ላይ ወታደሮች ደጋግመው በተኮሱባቸው ጥይት ሽንጣቸውንና አናታቸውን ተመትተው ተገድለዋል። ሰመጉ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎችንም ዝርዝር ይዞ ወጥቷል።
የሰመጉን ሪፖርት ዝርዝር መረጃ በቅርቡ የምናስተላልፈው መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።