ግንቦት ፳፩ ( ሃያ አንድ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በባህርዳር ከተማ የተለያዩ ጥቃቶች እንደሚፈጸሙ የሚገልጹት ነዋሪዎች፣የጥቃቱን ፈጻሚዎች ማንነት ለማወቅ አለመቻሉ ግራ አጋብቷቸዋል፡፡ የክልሉን ደህንነት እንቅስቃሴ በበላይነት የሚመራው የህውሃት ደህንነት ክፍል ጥቃቶችና አፈናዎችን መመከት አለመቻሉን የከተማዋ ነዋሪኦች ለክልሉ ወኪላችን ገልጸውላታል።
ሰሞኑን በባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ላይ የተካሄዱትን ግድያዎችና አፈናዎች መመከት ያልቻለው የደህንነት ኃይሉ፣ ፖሊስ ወንጀሉን የፈጸሙትን ግለሰቦች መያዝ ሲገባው ወንጀሉ በተፈጸመበት አካባቢ የሚገኙ ወጣቶችን ያለምንም ማስረጃ በጅምላ በማፈስ ወደ አስር ቤት መወርወሩ እንደሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡
በባህር ዳር ከተማ ግንቦት ሃያ ክፍለ ከተማ ከአራት ቀን በፊት በሰው እጅ ተገድሎ በተገኘ ግለሰብ ምክንያት በርካታ ወጣቶች በ9ኛ ፖሊስ ጣቢያ የታሰሩ ሲሆን ወደ ፍርድ ቤት ቢቀርቡም የዋስትና መብታቸው ተገፎ በእስር ላይ እንዲቆዩ መደረጉ እንዳሳዘናቸው የወጣቶቹ ቤተሰቦች ለዘጋቢያችን ገልጸዋል፡፡
በባህር ዳር ከተማ የሚገኘው የብሉ ናይል ኮሌጅ ባለንብረት ወንድ ልጅን በማፈን ሁለት ሚሊዮን ብር እንዲከፍሉ ያስገደዱት ማንነታቸው ያልታወቁ ግለሰቦች ከሶስት ቀን በላይ ልጁን አፍነውት ቢቆዩም ፤ በከተማዋ የደህንነት ክፍሉን የሚቆጣጠሩት የህውሃት ሰዎች አፋኞችን ለመያዝ ያደረጉት ጥረት አለመሳካቱን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች ተናግረዋል፡፡
የህውሃት የደህንነት ሰዎች የክልሉን ጸጥታ ዘርፍ ሰዎች እና ፖሊሶችን በመያዝ በገንዘብ ርክክቡ ወቅት አፋኞችን ለመያዝ ያደረጉት ጥረት የመረጃ ክፍሉ በሰራው ስህተት ሊከሽፍ እንደቻለ በጸጥታ ዘርፉ ስር የሚገኙ አባሎች ለዘጋቢያችን ጠቁመዋል፡፡
የገንዘብ ዝውውሩ በሚካሄድበት ቀን በቅብብሉ ቦታ የተገኙት የደህንነት ኃይሎች ሆን ተብሎ አጠራጣሪ በሚመስል ሁኔታ በአካባቢው መታየታቸው አፋኞችን ለመያዝ የተደረገውን ሙከራ እንዳከሸፈው ታውቋል፡፡ከአፋኞች ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የሚጠረጥሩት የክልሉ የደህንነት አባላት፣ አፋኞች አስቀድመው ስለክትትሉ ማወቃቸው ተዓምር ሆኖባቸዋል፡፡
አፋኞች ከሶስት ጊዜ በላይ ቦታ በመቀያየር የጠየቁትን ገንዘብ ከደህንነት አባላት በተሰወረ መልኩ ከባለ ሃብቱ በመረከብ አድራሻቸውን ለማጥፋት እንደቻሉ በኦፕሬሽኑ የተሳተፉ የደህንነት አባላት ለዘገቢያችን ጠቁመዋል፡፡