የጎርፍ አደጋ በረሃብ የተጎዳውን ህዝብ ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉን ተመድ አስታወቀ

ግንቦት ፳፩ ( ሃያ አንድ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባወጣው መረጃ በኢትዮጵያ ከ3 ሳምንት በፊት በኦሮምያ በምዕራብ ሃረርጌ በሃዊ ጉዲና ወረዳ እና በአርሲ ዞን ሰሩ እና ጮሌ ወረዳዎች የጣለው ዝናብ በርካታ ዜጎችን አፈናቅሏል።

በምዕራብ ሃረርጌ ዞን በሃዊ ጉዲና ወረዳ 8 ሰዎች በጎርፍ አደጋ ሲሞቱ 5ቱ ደግሞ ቆስለዋል። 3 ሺ 179 የቀንድ ከብቶች አልቀዋል። በአርሲ ዞን ሰሩ ወረዳ ደግሞ 1500 ሰዎች ፣ በጮሌ ወረዳ ደግሞ 405 ሰዎች ተፈናቅለዋል። 17 ቤቶችም ወድመዋል።
ጎርፉ በአገሪቱ የተረጅዎችን ቁጥር ወደ 10 ሚሊዮን 200 ሺ እንዳሻቀበው ድርጅቱ አስታውቋል።