ኢሳት (ግንቦት 18 ፥ 2009)
በቅርቡ ለግል የልማት ፕሮጄክቶች ሲሰጥ የቆየውን ብድር ያቋረጠው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ለግብርና ዘርፍ ለስራ ማስኬጃ የሚሰጠውን ብድር አቋረጠ።
ባንኩ የወሰደው ይኸው ተጨማሪ ዕርምጃ በተያዘው የክረምት ወር ብድርን ወስደው በግብርና ምርት ላይ ሲሰማሩ ለነበሩ ባለሃብቶች ያልታሰበ ድንጋጤ ማሳደሩን ካፒታል የተሰኘ የቢዝነስ ጋዜጣ ዘግቧል።
የብሄራዊ ባንክ ከቀናት በፊት ተግባራዊ ያደረገው ይኸው መመሪያ የብድር ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቶ ገንዘብ ለመቀበል በዝግጅት ላይ ያሉ ባለሃብቶችን መጉዳቱ ታውቋል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ባለፈው ወር ለግል የልማት ባንኮች ሲሰጥ የቆየውን ብድር በማቋረጥ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የብድሩን ጥያቄ እንዲያስተናግድ ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወሳል።
ይሁና ለባንኩ የብድር ጥያቄን አቅርበው ምላሽን በመጠባበቅ ላይ የነበሩ በርካታ ባለሃብቶች በባንኩ የተወሰደው ዕርምጃ ተፅዕኖ እንዳሳደረባቸው ሲገልጹ ቆይተዋል።
በአማራ፣ ቤኒሻንጉል፣ አፋር፣ ጋምቤላ፣ ኦሮሚያ፣ እንዲሁም በትግራይ ክልሎች በግብርና ዘርፍ ተሰማርተው ብድር በመጠባበቅ ላይ ያሉ ባለሃብቶች የብድር ጥያቄያቸውን በተመሳሳይ መልኩ ለልማት ባንክ እንዲያቀርቡ ታዘዋል።
ባለሃብቶቹ በሰሊጥ፣ በቆሎና የጥጥ ምርት ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ሲሆን የብሄራዊ ባንክ የወሰደው ዕርምጃ ጊዜያዊ እንደሆነ ተነግሯል።
ይሁንና ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የባንኩ አካላት ውሳኔውን በቋሚነት ለማስቀጠል ጉዳዩ በሚመለከታቸው አካላት ዘንድ ምክክር እየተካሄደ መሆኑን ግዜጣው አመልክቷል።
የብድር ጥያቄ አቅርበው ጉዳያቸው በመታየት ላይ የነበረ ባለሃብቶች በበኩላቸው ባንኩ ሊፈጠር የሚችለውን ክፍተት ተረድቶ በልዩ ሁኔታ እንዲያስተናግዳቸው ጥያቄ ቢያቀርቡም ምላሽ አላገኙም።
የብድር ጥያቄያቸው አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ የሚገኘው ባለሃብቶች ለኢትዮጵያ ልማት ባንክ የብድር ጥያቄን አቅርቦ ምላሽን ለማግኘት እስከ ስድስት ወር እንደሚፈጅና አሰራሩ በግብርና ስራቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን እንደሚያሳደር አክለው አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ተግባራዊ ያደረገውን አዲስ የብድር አሰራር በተመለከተ ዝርዝር መረጃን ይሰጣል ቢባልም እስከ አሁን ድረስ የተሰጠ ተጨማሪ ማብራሪያ የለም።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች በበኩላቸው ባንኩ ተግባራዊ ያደረገው አዲስ መመሪያ በባለሃብቶች ዘንድ ግራ መጋባትን ፈጥሮ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በጋምቤላ ክልል ለሰፋፊ የእርሻ መሬት ለሃገር ውስጥና ለውጭ ባለሃብቶች ሲሰጥ በቆየው ብድር በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ኪሳራ ደርስቦበት እንደነበር የሚታወስ ነው።
ባንኩ የደረሰበትን ይህንኑ ኪሳራ ተከትሎ መንግስት የመሬትና የብድር አቅርቦት ለአንድ አመት ያህል እንዲቋረጥ አድርጎ የቆየ ሲሆን፣ ከወራት በፊት መሬትን የማስተዳደሩ ስልጣን ለጋምቤላ ክልል ተላልፏል ተብሎ ብድርና መሬት የማቅረቡ ስራ እንዲቀጥል ተደርጓል። ይሁንና በርካታ ባለሃብቶች የፌዴራሉ መንግስት ወስዶ የነበረው ዕርምጃ ኪሳራ አስከትሎብናል በማለት ቅሬታ እያቀረበቡ መሆናቸው ታውቋል።