ግንቦት ፲፮ ( አሥራ ስድስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአፋር ክልል የምትገኘውን የብዓላ ወረዳን ወደ ትግራይ ክልል ለማካለል ሕወሃት የልዩ ወረዳ መብት እንዲፈቀድለት ጥያቄ አቅርቧል። የወረዳዋ ነዋሪ የሆኑ የትግራይ ብሔር ተወላጆች ነባር ነዋሪ የሆኑትን የአፋር ብሄር ተወላጆች በማግለል የስልጣን እና የሃብት ቅርምቱን በበላይነት ተቆጣጥረዋል።
ባለፉት 26 ዓመታት ውስጥ በክልሉ በተለይም በጨው ምርታቸው በሚታወቁት አፍዴራ፣ ዳሉል፣ ኤርታአሌ፣ ፖታሽ፣ የኮናባ የወርቅና ማእድን ማውጫ ቦታዎች በህወሃት ባለሃብቶች መዳፍ ወድቀዋል።
የንግድ፣ የቱሪዝም ገቢውን በብቸኝነት የያዙት የስርዓቱ ባለሃብቶች ለጉልበት ሥራም የአካባቢውን ተወላጆች ከማሰራት ይልቅ ከትግራይ ክልል ነዋሪዎችን በማምጣት የሕዝብ ቁጥሩን ሆን ተብሎ እንዲጨምር ተደርጓል። ሁለት የአፋር ክልል ወረዳዎች ከሕዝብ ፈቃድ ውጪ በግዴታ ላለፉት 17 ዓመታት ወደ ትግራይ እንዲካለሉ መደረጉን የአፋር ሕዝብ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ወጣት አካድር ኢብራሂም ተናግሯል።
የብዓላ ወረዳ የልዩ ወረዳ መብት እንዲሰጠው ለፌደሬሽን ምክር ቤት ያቀረቡት ጥያቄ በምክር ቤቱ ውድቅ ቢደረግም ፣ የወረዳዋ የትግራይ ተወላጆች ከአፋርኛ እና አማርኛ ውጭ ትግርኛ መማር እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል። “ካለፍቃዳቸው ወደ ትግራይ ክልል የተካለሉት ወልቃይቶች፣ ኩናማዎችና ኢሮቦች በግዴታ ትግርኛ እንዲማሩ እየተደረገ እንዴት በአፋር ክልል የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች አፋርኛ አንማርም፣ የምንማረው በትግርኛ ነው’ ሊሉ ቻሉ በማለት ነዋሪዎቹ ይጠይቃሉ። የማንነት ጥይያቄዎች በትግራይ በኩል ሲመጡ ፌደሬሽን ምክርቤት በአፋጠኝ የሚያየው መሆኑና ሌሎች ብሄረሰቦች ግን ምክር ቤት በር ላይ እንኳን ለመድረስ አለመቻላቸውን በማስታወስ ምክር ቤቱ የህወሃትን ጥያቄ በሂደት ስልታዊ በሆነ መንገድ እያስተናገደው ነው በማለት ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
በኢትዮጵያ ማንነታችን ይከበር በማለት ለአመታት የጠየቁ የወልቃይት፣ የወለኔ፣ የቁጫ፣ የዶርዜ፣ የዛይ እና ጋሮ ማህበረሰቦች እስካሁን መፍትሔ አላገኙም። የብሄረሰቦቹ ተወካዮች፣ ጥያቄ በማንሳታቸው ከግድያ ጀምሮ የተለያዩ እርምጃዎች ተወስዶባቸዋል። በቋንቋ ላይ የተመሰረተው የፌደራል ስርዓቱትበተለያዩ የአገሪቱ ክልል ለሚነሱት ግጭቶች መንስኤ እየሆነ መምጣቱን የመስኩ ባለሙያዎች በመግለጽ ላይ ናቸው።