ግንቦት ፲፮ ( አሥራ ስድስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከታህሳስ 15/2008 ዓ.ም ጀምሮ በእስር ላይ የሚገኘው የነገረ ኢትዮጵያ ዋና አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ግንቦት16 ቀን 2009 ዓም በዋለው ችሎት ጥፋተኛ የተባለ ሲሆን፣ የቅጣት ውሳኔውን ግንቦት18፣ 2009 ዓም እንደሚሰማ ተነግሮታል።
ፍርድ ቤቱ ፣ ጋዜጠኛው ከተለያዩ የሰማያዊ አባላት መረጃ በመሰብሰብ ኢሳት ለተሰኘ የቴሌቭዥን ጣቢያና ለግንቦት7 አመራሮች ማስተላለፉን ጠቅሷል።
ጋዜጠኛው መጀመሪያ ላይ ከቀረበበት የሽብር ክስ ነጻ ተብሎ በመደበኛ የወንጀል ህግ አንቀጽ 257 መተላለፍ ጋር በተያያዘ ጥፋተኛ የተባለ ሲሆን፣ አንቀጹ ዋስትና ባያስከለክልም ከፍተኛ ፍርድ ቤት ግን ዋስትና ከልክሎታል። በዛሬው ችሎት ፍርድ ቤቱ ጋዜጠኛው የቅጣት ማቅለያ ያቀርብ እንደሆነ ሲጠይቀው፣ ጋዜጠኛ ጌታቸው የተወሰነውን ለመቀበል ዝግጁ በመሆን የቅጣት ማቅለያ ለማቅረብ ፈቃደኛ አለመሆኑን ገልጿል።
ጋዜጠኛ ጌታቸው ነገረ ኢትዮጵያ ላይ ይሰራ በነበረበት ወቅት በመላው አገሪቱ የሚካሄዱ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ሲያጋልጥ ቆይቷል። በስራው ላይ እያለ የተለያዩ ማስፈራሪያዎችም ይደርሱት ነበር።
ጋዜጠኛ ጌታቸው በመሰናዘሪያ ጋዜጣና በላይፍ መጽሔት በአምደኝነት ሰርቷል።