ኢሳት ( ግንቦት 16 ፥ 2009)
የሳውዲ አረቢያ መንግስት ህጋዊ የመኖሪያ የስራ ፈቃድ የሌላቸው ሰዎች ከሃገሪቱ እንዲወጡ ባስተላለፈው አዲስ መመሪያ ከ700 ሺ የሚበልጡ ኢትዮጵያውያን አደጋ እንደተጋረጠባቸው የአለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (IOM) አስታወቀ።
ሃገሪቱ ያስቀመጠችው የ90 ቀናት የምህረት ቀን በሰኔ ወር መጨረሻ ላይ የሚጠናቀቅ ቢሆንም፣ እስካለፈው ሳምንት ድረስ 8 ሺ 400 ኢትዮጵያውያን ብቻ ወደ ሃገራቸው ሊመለሱ መቻላቸውን ለመረዳት ተችሏል።
ከሳውዲ አረቢያ ባልወጡ ኢትዮጵያውያን ስጋት እንዳደረበት የገለጸው የስደተኞች ድርጅት በአጠቃላይ ወደ 700 ሺ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን በመመሪያው ተጎጂ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይፋ አድርጓል።
እነዚሁ ኢትዮጵያውያን እስከ ሰኔ 21 2009 ቀን አም ከሳውዲ አረቢያ የማይወጡ ከሆነ እስራትን ጨምሮ የተለያዩ አንግልቶች ሊደርስባቸው እንደሚችል ድርጅቱ ስጋቱን ገልጿል። ሃገሪቱ ያስመቀመጠችው የጊዜ ግደብ ሊጠናቀቅ ወደ 41 ቀናት ብቻ ቢቀሩትም ወደ ሃገር የተመለሱ ኢትዮጵያውን ቁጥር እጅግ አነስተኛ መሆኑ ተመልቷል።
የሳውዲ አረቢያ ባለስልጣናት በበኩላቸው የጊዜ ገደቡ ከተጠናቀቀ በኋላ ከሃገሪቱ መውጣት ያለባቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለማስወጣት በሚቻልበት ዘመቻ ዙሪያ ማክሰኞ ምክክር መጀመራቸውን ሳውዲ ጋዜት ዘግቧል።
እስካሁን ድረስ 225ሺ አካባቢ የሚሆኑ የተለያዩ ሃገራት ዜጎች ሃገሪቱን ለቀው ለመውጣት ፈቃደኝነትን ያሳዩ ሲሆን፣ 49ሺ የሚሆኑ ከሳውዲ አረቢያ መውጣታቸውን ለመረዳት ተችሏል።
የሳውዲ አረቢያ የሃገር ውስጥ ሚኒስቴር ባለስልጣናት የተቀመጠው የ90 ቀን የጊዜ ገደብ መጠናቀቁን ተከትሎ የቤት ለቤት ፍተሻን ጨምሮ ሌሎች ዕርምጃዎች እንደሚወስዱ ለመገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።
በሚኒስቴሩ የጸጥታ ጉዳዮች ሃላፊ የሆኑት ሚጀር ጄኔራል ጃማን አልጋምዲ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሃገሪቱ ዜጎችና የንግድ ተቋማት መመሪያን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጥብቅ ትዕዛዝ መተላለፉን ለሳውዲ ጋዜጥ ገልጸዋል። ሃገሪቱ ከሶስት አመት በፊት ባካሄደችው ዘመቻ ወደ 150 ሺ አካባቢ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን እንዲወጡ መደረጉ ይታወሳል።
የአለም አቀፍ ስደተኛ ድርጅት (IOM) እንዲሁም በተለያዩ የአለማችን ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያን በሳውዲ አረቢያ የጸጥታ ሃይሎች የተወሰደውን ድብደባና እንግልት በማውገዝ አለም አቀፍ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ማካሄዳቸውም ይታወሳል።
ኢትዮጵያውያኑ ወደ ሃገር ለመመለስ ለተደረገው ጥረትም ከ100 ሺ ዶላር በላይ ተሰብስቦ ለስደተኛ ድርጅቱ ተሰጥቷል።