ኢሳት (ግንቦት 15 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ በተፈጸመው የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች እጃቸው አለበት የሚባሉት እና በገዢው የህወሃት የአመራር ስልጣን ከፍተኛ ሃላፊነት ያላቸው ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተመረጡ።
ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር በነበሩ ጊዜ የኮሌራ በሽታ እንዲደበቅ አድርገዋል በሚል በኒውዮርክ ታይምስና በዋሽንግተን ፖስት ጋዜጦች ዘገባዎች ሲቀርቡባቸው እንደነበር ይታወሳል።
የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ለመሆን ሲያካሄዱ በነበረው ዘመቻም በህወሃት/ኢህአዴግ የሚመራው መንግስታቸው በሚሊዮን የሚቆጠር እገዛ ሲያደርግላቸው እንደነበር አይዘነጋም።
ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም በአፍሪካ አባል ሃገራት ድጋፍ እንዲያገኙ ሁኔታው ተመቻችቶላቸው ወደ ምርጫው መግባታቸው ይታወቃል።
በመጨረሻም ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም በአለም ጤና ድርጅት አባል ሃገራት ጠቅላላ ጉባዔ በመጀመሪያው ዙር 95 ድምፅ በማግኘት ለቀጣዩ ዙር አልፈዋል። የብሪታኒያው ተወካይ ዶ/ር ዴቪድ ናባሮም 52 አምፅ አግኝተው ለሁለተኛ ዙር አልፈው ነበር።
የፓኪስታኗ ተወካይ ግን 38 ድምፅ ብቻ በማግኘታቸው ከመጀመሪያው ዙር ውድድር ከወዲሁ ተሰናብተዋል።
በድርጅቱ ህግ መሰረት ሁሉም ተወዳዳሪዎች 2/3 ኛ ድምፅ ባለማግኘታቸው ወደ ሁለተኛው ዙር ውድድር ተገብቶ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም 121 ድምፅ ሲያገኙ ዶ/ር ዴቪድ ናባሮ 68 ድምፅ አግኝተዋል።
ይህም ሆኖ ዶ/ር ቴዎድሮስ 2/3ኛ ድምፅ ለማግኘት 1 ድምፅ ባያገኙም በአብላጫው ድምፅ መሰረት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃሞም የአለም ጤና ድረጅት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተመርጠዋል።