ኢሳት (ግንቦት 15 ፥ 2009)
በጋምቤላ ክልል በማጃንግ ዞን ስር በሚገኙ አራት ቀበሌዎች የወባ በሽታ ወረርሽኝ መቀስቀሱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይፋ አደረገ።
በማጃንግ ዞን በመንገሺ ወረዳ በመሰራጨት ላይ ባለው በዚሁ ወረርሽኝ እስከአሁን ድረስ ከ550 የሚበልጡ ሰዎች ለህመም መዳረጋቸውንና በሽታው ወደ አጎራባች ቀበሌዎች ይዛመታል የሚል ስጋት ማሳደሩን ድርጅቱ በክልሉ ያለውን የበሽታውን ስርጭት አስመልክቶ ባወጣው ሪፖርቱ አመልክቷል።
በእስካሁኑ የበሽታው ስርጭት የሞተ ሰው ሪፖርት ባይደረግም ዕድሚያቸው ከአምስት እስከ 14 አመት የሆነ ህጻናት በወባ በሽታው በአብዛኛው የተያዙ የህብረተሰብ ክፍል መሆናቸው ታውቋል።
የጋምቤላ ክልል ጤና ቢሮ የጤና ባለሙያዎችን በማሰማራት የበሽታውን ስርጭት ለመግታት ጥረት እያደረገ ሲሆን፣ ለተጨማሪ የሰብዓዊ ድጋፍ ጥሪ ማቅረቡንም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዕርዳታ ማስተባበሪያ መምሪያ ገልጿል።
የጋምቤላ ክልል በኢትዮጵያ የወባ በሽታ በየአመቱ በርካታ ሰዎችን ከሚገድልባቸው አካባቢዎች አንዱ መሆኑን መረጃዎችን ያመለክታሉ። በኢትዮጵያ ወደ 45 ሚሊዮን አካባቢ የሚሆኑ ሰዎች ለወባ ተጋላጭ በሆኑ ስፍራዎች እንደሚኖሩ የአለም ጤና ድርጅት (WHO) ይገልጻል።
ላለፉት አስርተ አመታት የበሽታን ስርጭት ለመቀነስ መጠነ ሰፊ ዘመቻ ሲካሄድ ቢቆይም የወባ በሽታ አሁንም ድረስ በሃገሪቱ የጤና ችግር ሆኖ መቀጠሉ ይነገራል። ይህ በእንዲህ እንዳለም፣ ባለፈው ሳምንት በጋምቤላ ክልል የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በተከሰተ ከባድ የጎርፍ አደጋ በጋምቤላ ከተማ 05 ቀበሌ ነዋሪ የሆነ የአምስት አመት ህጻን ማለፉን የእርዳታ ማስተባበሪያ መምሪያው አክሎ ገልጿል።
በከተማዋ ከሚገኙት ቀበሌዎች መካከል ቀበሌ 01 ፥ 03 ፥ እና 05 በጎርፉ አደጋ ክፉኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፣ 600 የቤተሰብ አባላት ለከፋ ችግር ተጋልጠው እንደሚገኙም ለመረዳት ተችሏል።
የክልሉ መንግስትና የዕርዳታ ድርጅቶች ከቀያቸው ተፈናቅለው የሚገኙትን እነዚሁኑ ነዋሪዎች መጠለያና የምግብ አቅርቦት ለመስጠት ርብርብ እያደረጉ መሆኑንም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አክሎ አስታውቋል።
ከወራት በፊት ከሱዳን ዘልቀው ወደ ክልሉ የገቡ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት በትንሹ 28 ነዋሪዎች ተገድለው በርካታ ሰዎች ደግሞ ከቀያቸው መፈናቀላቸው ይታወሳል።
በጎሳ ታጣቂዎች ተደጋጋሚ ጥቃት ስጋት ያደረባቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ለደህንነታቸው ሲሉ ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው እንደሚገኙ ሲገለጽ ቆይቷል። በጋምቤላ ክልል ያለው የተፈናቃዮች አጠቃላይ ቁጥር ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛና እየጨመረ በመሄድ ላይ መሆኑንም ለመረዳት ተችሏል።