ኢሳት (ግንቦት 15 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል ከ700 የሚበልጡ ሰዎች በአጣዳፊ ተቅማትና ትውከት በሽታ ህይወታቸው ማለፉን የአለም ጤና ድርጅት አስታወቀ።
መንግስት በሽታው ኮሌራ አይደለም ቢልም የአለም ጤና ባለሙያዎች የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታው ኮሌራ ስለመሆኑ የላቦራቶሪ ውጤት መገኘቱን እንዳረጋገጡ ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ባለፈው ሳምንት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
ይሁንና የአለም ጤና ድርጅት የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት ክስተት ሲል በገለጸው ወረርሽኝ ባለፉት አራት ወራቶች በክልሎች 776 ሰዎች መሞታቸውን ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል።
በሶማሌ ክልል ስር በሚገኙ በርካታ ቀበሌዎች በመዛመት ላይ ባለው በዚሁ በሽታ አጠቃላይ 32ሺ 689 ሰዎች በሽታው ተጠቂ መሆናቸውም ታውቋል።
በድርቅ ጉዳይ ደርሶባቸው ካሉ አካባቢዎች 91 በመቶ የሚሆነው የበሽታው ወረርሽኝ በዚሁ የሶማሌ ክልል የተከሰተ ሲሆን፣ 99 በመቶ የሚሆነው የሞት አደጋም በክልሉ መድረሱን የአለም ጤና ድርጅት ገልጿል።
አለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶች መንግስት በሽታው ኮሌራ ተብሎ እንዳማይጠራና የበሽታው የስርጭት መጠን ለህዝብ ይፋ እንዳይሆን ጫና ሲያደርግ መቆየቱን ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ አስረድተዋል።
እነዚሁ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የእርዳታ ድርጅቶች ለወራት በሶማሌ ክልል ጉዳት ሲያደርግ የቆየው የበሽታ ስርጭት ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸዋል።
የአለም ጤና ድርጅት በበኩሉ የ77ቱ ሰዎች ሞት ከጥር ወር እስከሚያዚያ ወር ድረስ ብቻ ያለውን አህዝ እንደሚያመለክት በሪፖርቱ አስፍሯል።
የክልሉና የፌዴራል ባለስልጣናት የበሽታ ወረርሽኙ በሰው ላይ ጉዳት ማድረሱን ቢያረጋግጡም ትክክለኛ የሟቾች ቁጥር ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
የጤና ድርጅቱ በበሽታው የሞቱ ሰዎችን አስመልክቶ ባወጣው መረጃ ላይ መንግስትም ሆነ የክልሉ መንግስት የሰጡት ምላሽ የለም።
የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት የተመረጡት ዶ/ር ቴዎድሮስ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሆነው ባገለገሉበት ጊዜ በተለያዩ ጊዜያት የተከሰቱ ሶስት የኮሌራ በሽታዎችን ደብቀዋል ተብለው በአለም የጤና ባለሙያዎች ቅሬታ እንደቀረበባቸው ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ባለፈው ሳምንት ሰፊ ዘገባ ማቅረቡ ይታወሳል።