ግንቦት ፲፬ ( አሥራ አራት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጽ/ቤት ፊት ለፊት በተካሄደው ተቃውሞ ኢትዮጵያውያን ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የአለም የጤና ድርጅት ሆነው ለመጨረሻው ዙር ውድድር መቅረባቸውን በከፍተኛ ሁኔታ ተቃውመዋል። ዶ/ር ቴዎድሮስ እና እርሳቸው የሚወክሉትን የህወሃት /ኢህአዴግ አገዛዝ ፖሊሲዎችና በስልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ የሰሩዋቸውን ወንጀሎች እየጠቀሱ ውግዘታቸውን አሰምተዋል።
ከለንደን ወደ ጀኔቫ በመሄድ ሰልፉን ሲያስተባብሩ ከነበሩት መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ዘላለም ተሰማ፣ ጉባኤውን የሚመሩት ተወካዮችና የአባል አገራት ተወካዮች በተገኙበት ወቅት የዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ስም ሲነሳ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው “ ዶ/ር ቴዎድሮስን ብትመርጡ ለሰብአዊነት ሃፍረት ነው ፣ አፍሪካ አስቢ፣ ይህን ሰው መምረጥ ክስረት ነው “ በማለት ተቃውሞ በማሰማት፣ መሪዎች ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖምን እንዳይመርጡ ጠይቀዋል። አቶ ዘላለም በጸጥታ ጠባቂዎች እንዲወጡ ቢደርግም፣ መልእክታቸውን በበቂ ሁኔታ ማስተላለፋቸውን ለኢሳት ገልጸዋል።
በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ከተገኙት ኢትዮጵያውያን መካከል ወ/ሮ ጫልቱ አብዲአህመድ አንዷ ሲሆኑ፣ ሰልፉ ከጠበቁት በላይ መሆኑንና በአንድነት ሆነው ድምጻቸውን ማሰማታቸውን ገልጸዋል።
ዶ/ር ቴዎድሮስ ኢትዮጵያዊ ስለሆነ ለምን ትቃወሙታላችሁ በማለት የገዢው ፓርቲ ደጋፊዎች አስተያየት ሲሰጡ ይሰማል፣ በዚህ አስተያየት ላይ ምን ትያለሽ ተብለው ለተጠየቁት ወ/ሮ ጫልቱ ሲመልሱ፣ “ቴዎድሮስ ኢትዮጵያዊ አይደለም፣ ህዝብን የሚገድልና የሚያስጨፈጭፍ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ስላለው ብቻ ኢትዮጵያዊ ሊሆን አይችልም” ብለዋል ።