ኢሳት (ግንቦት 11 ፥ 2009)
ኢትዮጵያ፣ሩሲያና ግብፅ በአለማችን ካሉ ሃገራት መካከል በሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት ላይ ስልታዊ አፈናን ከሚፈጽሙ ሃገራት ግንባር ቀደም ሆነው መገኘታቸውን አንድ አለም አቀፍ ድርጅት ይፋ አደረገ።
የሶስቱ ሃገራት መንግስታት ተቋማቱ ስራቸውን በአግባቡ እንዳይወጡ ለማድረግ የተለያዩ ፖለቲካዊ እና ስልታዊ ማዋከቦችን እየፈጸሙባቸው እንደሚገኝ ካርኒግ ኢንዶውመንት ፎር ኢንተርናሽናል ፒስ የተሰኘው ተቋም በጉዳዩ ዙሪያ ያካሄደውን ጥናት ዋቢ በማድረግ አስታውቋል።
ኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማትን የሚቆጣጠር “አፋኝ” የተባለ ህግ ከስድስት አመት በፊት ተግባራዊ ያደረገችን ሲሆን፣ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረትና በርካታ አካላት አዋጁ ሲቃወሙት ቆይተዋል።
መንግስት በስራ ላይ አውሎት ባለው በዚሁ አዋጅ መሰረት በዴሞክራሲና በምርጫ ትምህርት ዙሪያ የሚሰራ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ስራቸውን እንዲያቆሙ መደረጋቸው ይታወሳል።
በዚሁ የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት መብት ዙሪያ ሪፖርቱን ይፋ ያደረገው አለም አቀፍ ድርጅቱ፣ የኢትዮጵያ፣ የሩሲያና የግብፅ መንግስታት እነዚሁ ድርጅቶች ተልዕኳቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ ለማድረግ ጥብቅ እና አፋኝ የተባሉ ህጎችን ተግባራዊ አድርገው እንደሚገኙ አመልክቷል።
በኢትዮጵያ በመብት መከበር ጉዳይ ላይ እንዳይሰሩ የተደረጉ በርካታ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ስራቸውን ወደ አገልግሎት መስጫ ቀይረው የሚገኙ ሲሆን፣ በሚያገኙት ድጎማ እና ድጋፍ ላይም ከፍተኛ ቁጥጥር እንደሚደረግባቸው ካርኔግ ኢንዶውመንት ፎር ኢንተርናሽናል ፒስ የተሰነው ተቋም አብራርቷል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶቹ ላይ የተጣለው ይኸው እገዳና ቁጥጥር በሃገሪቱ የሰብዓዊ መብት እንዳይከበርና ዲሞክራሲ እንዳይጎለብት ቀጥተኛ ጫና ማሳደሩንም ከሪፖርቱ ለመረዳት ተችሏል።
በኢትዮጵያ በ1997 አም የተካሄደውን ብሄራዊ ምርጫ ተከትሎ ተግባራዊ ተደርገው የሚገኙት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና የሽብር ወንጀል ህጎች በተለያዩ አካላት ዘንድ ተቃውሞ ሲቀርብባቸው ቆይቷል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ሂውማን ራይትስ ዎች፣ እንዲሁም የአውሮፓ ፓርላማ እና ሌሎች አካላት ህጎቹ በተለይ የተቃዋሚ አመራሮችን፣ ጋዜጠኞችንና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማትንና ግለሰቦችን ለማዋከብና ለማሰር እያገለገለ መሆኑን ይገልጻሉ። በተለይ የጸረ-ሽብር አዋጁ በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች መታሰር ምክንያት መሆኑን እነዚሁ ተቋማት ሲገልጹ ቆይተዋል።
ከኢትዮጵያ ጋር የተፈረጁት ሩሲያና ግብፅም በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ላይ ተመሳሳይ ድርጊት እንደሚፈጽሙና ሃገሪቱ በአለማችን ካሉ ሃገራት መካከል አፈናዎችን በመፈጸም ግንባር ቀደም ሆነው መፈረጃቸውን ሪፖርቱ አክሎ አመልክቷል።