ግንቦት ፲፩ ( አሥራ አንድ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ጋዜጠኛ ብሩክ እንዳለ ዛሬ በፌስ ቡክ ገጹ ላለፉት አራት ዓመታት ከኢቢሲ ጋር ደጉንም መልካሙን ግዜ መካፈሉን በመጥቀስ፤ “ሰሞኑን ከቴዲ አፍሮ ጉዳይ ጋር ተያይዞ በተከሰተው ነገር ግን ከህሊናዬ ጋር እየታገልኩ ልቀጥል አልችልም”ብሏል።
“ጉዳዩ እንድን የኪነጥበብ ሰው ማቅረብና ያለመቅረብ ጉዳይ ብቻ አይደለም”ያለው ጋዜጠኛ ብሩክ፤ ነገሩን የጋዜጠኝነትን ልዕልና የሚጋፋ ሆኖ ስላገኘውና ብዙዎች መሰዋት የከፈሉለትን ሙያ ክብር ለመስጠትም ጭምር ሲል እዚህ ውሳኔ ለይ መድረሱን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የመዝናኛ ፕሮግራም ባልደረባ የኾነው ብሩክ ባለፈው ሳምንት ነበር ወደ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን በመሄድ ኢትዮጵያ ተብሎ በሚጠራው የአርቲስቱ አልበም ዙሪያ ቃለ ምልልስ ያደረገው። ዕለቱኑ ከቃለ ምልልሱ ቀንጭቦ በዚያው በጣቢያው ባስተላለፈው የፕሮግራም ማስታወቂያ ቴዎድሮስ ካሳሁንን ከጠበቀው በላይ ሆኖ እንዳገኘውና ቆይታው ብዙ የተማረበት እንደሆነ የጠቀሰው ጋዜጠኛ ብሩክ፣ ሙሉ ቃለ ምልልሱን በእሁድ ፕሮግራም ይዞ እንደሚቀርብ ገልጿል። ይሁንና ብዙም ሳይቆይ ጋዜጠኛው ከአርቲስቱ ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ እንዳይተላለፍ ኢቢሲ ከበላይ ባለሥልጣናት ትዕዛዝ መቀበሉ ተሰምቷል።
ባለስልጣናቱ እንዳስተላለፉት ተእዛዝም ጋዜጠኛው ከአርቲስቱ ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ ሳይተላለፍ ቀርቷል።
“ያለፉትን ስድስት ቀናት በምን አይነት ሁኔታ ውስጥ እንዳሳለፍኩ የማውቀው እኔ ነኝ” የሚለው ጋዜጠኛ ብሩክ፤ ሁሉንም ግዜው ሲደርስ እናየዋለን ብሏል፡፡
እዚህ ውሳኔ ላይ ስደርስ -በጋዜጠኘነት ሙያ ውስጥ ያላችሁን፣ በየዩኒቨርሲቲዎች የጋዜጠኝነትን ትምህርት የምትማሩ ተማሪዎችንና የምታስተምሩ መምህራንን እንዲሁም ፣ መላው የኢትዮጵያን ህዝብን በህሊናዬ እያሰብኩ ነው ብሏል ጋዜጠኛ ብሩክ።
የጋዜጠኛውን ውሳኔ ተከትሎ በርካታ ኢትዮጵያውያን በፌስቡክ አድናቆታቸውንና ድጋፋቸውን እየገለጹለት ነው።