ኢሳት (ግንቦት 9 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል እየተባባሰ ያለው የድርቅ አደጋ ወደ ረሃብ ሊለወጥ እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አሳሰበ።
ካለፈው ወር ጀምሮ በክልሉ መጣል የነበረበት የበልግ ዝናብ በአብዛኛው ባለመጣሉ ምክንያት በአካባቢው ጉዳትን እያደረሰ ያለው የድርቅ አደጋ በመባባስ ላይ መሆኑን በድርጅቱ ስር የሚገኘው የረሃብ ቅድመ ትንበያ መምሪያ ገልጿል።
ይኸው የድርቅ አደጋ ወደ ረሃብ ለመድረስ አንድ ደረጃ ብቻ ወደሚቀረው ደረጃ አራት ላይ እስከ መስከረም ወር ድረስ ሊደርስ እንደሚችል ድርጅቱ በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።
በርካታ አለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች በተለይ በሶማሌ ክልል ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ ወደ ረሃብ ሊቀየር ይችላል ሲሉ ተደጋጋሚ ማሳሰቢያን ሲሰጡ ቆይተዋል።
የመንግስት ባለስልጣናት በበኩላቸው ድርቁ በሰው ህይወት ላይ ጉዳትን እንዳያደርስ ጥረት በመደረግ ላይ ነው ቢሉም፣ ድርቁን ተከትሎ በክልሉ በርካታ ወረዳዎች የተከሰተው የኮሌራ በሽታ ለሰዎች ሞት ምክንያት መሆኑ ይነገራል።
የሶማሌ ክልል ጤና ቢሮና የፌዴራል ባለስልጣናት የበሽታ ወረርሽኙ በነዋሪዎች ላይ ጉዳት ማድረሱን ቢያረጋግጡም የሟች ሰዎች ቁጥርን ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
በተለያዩ ቀበሌዎች በመሰራጨት ላይ ያለውን ወረርሽኝ ለመቆጣጠር ወደ 1ሺ 200 አካባቢ የጤና ባለሙያዎች እንዲሰማሩ የተደረገ ሲሆን፣ የበሽታው ስርጭት ግን ዕልባት ሊያገኝ አለመቻሉን መረጃዎች ያመለክታሉ።
መንግስትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ዕርዳታ የተጋለጡ ወደ ስምንት ሚሊዮን አካባቢ ኢትዮጵያውያን ለመታደግ ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር አካባቢ እንደሚያስፈልግ ጥሪ ቢያቀርቡም በቂ ምላሽ ሊገኝ አለመቻሉን ሲገልፅ ቆይቷል።
ከአለም አቀፍ ማህበረሰብ ሊገኝ የታቀደው የምግብና የገንዘብ ድጋፍ ሊገኝ ባለመቻሉም ድርቁ እየተባባሰ በመሄድ ላይ መሆኑ ተመልክቷል። በኦሮሚያ፣ አፋር፣ ደቡብና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ስር የሚገኙ በርካታ ዞኖች ዳግም በተከሰተው የድርቅ አደጋ ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑ ታውቋል።
ይኸው የድርቅ አደጋ እስከቀጣዩ አመት ድረስ ሊዘልቅ ይችላል የሚል ስጋትን ያሳደረ ሲሆን፣ ከመስከረም ወር በኋላ ያለው ሁኔታ ከሚገመተው በላይ ጉዳትን ሊያስከትል እንደሚችል የእርዳታ ድርጅቶች በመግለጽ ላይ ናቸው።
ከቀናት በፊት ኒዮ ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ የመንግስት ባለስልጣናት በሃገሪቱ የሚከሰቱ የበሽታ ወረርሽኞች እንዳይታወቁ ሲያደርጉ ቆይተዋል በማለት የጤና ባለሙያዎች በተለይ በዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ላይ ያቀረቡትን ተቃውሞ መዘገቡ ይታወሳል።