ባለፉት 9 ወራት የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ከባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ100 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ቅናሽ ማሳየቱ ተገለጸ

ኢሳት (ግንቦት 9 ፥ 2009)

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ያገኘው የውጭ ምንዛሪ ከባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ100 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ቅናሽ ማሳየቱ ተገለጸ።

ባንኩ በአጠቃላይ በአመቱ ለማግኘት ያቀደው የውጭ ምንዛሪ ከታቀደው በታች እንደሚሆን የተሰጋ ሲሆን፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተገኘው ወደ 3.3 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ከባለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር በ100 ሚሊዮን ዶላር መቀነሱን አዲስ ፎርቹን ጋዜጣ ዘግቧል።

ከተገኘው የውጭ ምንዛሪ ውስጥ 85 በመቶ የሚሆነው በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለቤተሰቦቻቸው ከላኩት ገንዘብ መገኘቱ ታውቋል።

የሃገሪቱ የውጭ ንግድ መቀነስ በውጭ ምንዛሪ ክምችቱ ላይ ጫናን ያሳደረ ሲሆን፣ በአስመጪነት ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች የውጭ ምንዛሪን ለማግኘት በትንሹ ስድስት ወር ለመጠበቅ መገደዳቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል።

የአለም ባንክና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ኢትዮጵያ ያጋጠማትን የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለመቅረፍ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያን ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባት አሳስበዋል።

የአለም ባንክ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ብር ከዶላር ጋር ያለው የመግዛት አቅም ቅናሽ መደረግ እንዳለበት ሃሳብ ቢያቀርቡም የብሄራዊ ባንክ ዕርምጃው ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበልጣል በማለት ሃሳቡን እንደማይቀበለው ምላሽን ሰጥቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የብሄራዊ ንግድ ባንክ የውጭ ምንዛሪን ማግኘት የሚፈልጉ አስመጪ ነጋዴዎች ሌተር ኦፍ ክሬዲት ለመክፈት መቶ በመቶ ተቀማጭ እንዲያስገቡ ያወጣውን መመሪያ ተከትሎ የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ በጥቂት ወራት ውስጥ በ59 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ በማደግ ወደ 347 ቢሊዮን ብር ከፍ ማለቱ ተመልክቷል።

ይሁንና የግል ባንኮች ባንኩ የወሰደው እርምጃ በተቀማጭ ገንዘባቸው ላይ ቅናሽ እንዲታይ ማደረጉን አስታውቀዋል።

በግል ባንኮች ገንዘባቸውን አስቀምጠው የነበሩ በርካታ ባለሃብቶች ገንዘባቸውን ከባንኮቹ በማውጣት ወደ ንግድ ባንክ ገቢ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ለመረዳት ተችሏል። የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች በበኩላቸው መንግስታዊው ባንክ የወሰደው ዕርምጃ በግል ባንኮች ላይ ተፅዕኖን ለማሳደር ያለመ መሆኑን ሲገልጹ ቆይተዋል።

የንግድ ባንክ በወሰደው በዚሁ አዲስ ዕርምጃ የግል ባንኮች ወደ አራት ቢሊዮን ተቀማጭ ገንዘብ ማጣታቸውንም ለመረዳት ተችሏል።

መንግስታዊ ባንኮች የውጭ ምንዛሪን ካስገኙ ግለሰቦች እስከ መኖሪያ ቤት ድረስ የሚያስገኝ ሽልማት ተግባራዊ ቢያደርግም የግል ባንኮች ድርጊቱ ህግን የጣሰ ተግባር እንደሆነ ሲገልጹ ቆይተዋል።