ግንቦት ፱ ( ዘጠኝ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከ5 ዓመታት በፊት ተጀምሮ በ2008 ዓም ይጠናቀቃል ተብሎ የተጀመረውና በአሁኑ ሰዓት ከ35 በመቶ ያልበለጠ ግንባታ ያካሄደው እንዲሁም ከተፈጥሮ ውድመት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ተቃውሞ ሲቅርብበት የቆየው ያዩ የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ በመጀመሪያ የተያዘለት የ9 ቢሊዮን 600 ሺ ብር በጀት እንደማይበቃው ግንባታውን በሚያካሂደው በመከላከያ ኢንጂነሪንግ በኩል ጥያቄ አቅርቧል። ኩባንያው ተጨማሪ 4 ቢሊዮን 400 ሚሊዮን ብር እንደሚፈልግ የገለጸ ሲሆን፣ በመጀመሪያ የተያዘለትን ገንዘብ እስካሁን በአግባቡ ለምን እንዳልተጠቀመበት እንዲሁም ፕሮጀክቱ ለምን እንደዘገየ የተለያዩ ምክንያቶችን እየሰጠ ነው።
በጄ/ል ክንፈ ዳኘው የሚመራው ሜቴክ በአምስት አመት እቅዱ ላይ፣ ያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ የዘገየው የፋይናንስ ክፍያና በውል ስምምነቱ ዙሪያ የባለድርሻ አካላት የጋራ የማዳበሪያ ፋብሪካ ዲዛይን የአገር ዓቅም መደረጉ፣ አብዛኞቹን መሳሪያዎች አገር ውስጥ ማምረት የሚያስችል ቴክኖሊጂ መቀረጹ፣ እና ክስኳር ፋብሪካ ግንባታ ተይይዞ የተመጋጋቢና የተቀናጀ ፕሮጀክት አፈጻጸም ዝግጅት መደረጉ የሚሉ ምክንያቶችን አቅርቧል። በቅርቡ የፓርላማ አባላት ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ደግሞ ስራ አስኪያጁ ፕሮጀክቱ የዘገየው በካሳ ክፍያ መጓተትና ህብረተሰቡን የማግባባት ስራ በመሰራቱ ነው የሚል አዲስ ምክንያት ሰጥተዋል። ለገንዘቡ መጨመር ዋናው ምክንያት የፕሮጀክቱ መዘግየት ነው ሲሉ የፓርላማ አባላቱ ተናግረዋል።
በኢሉባቡር ዞን በያዩ ወረዳ የሚገነባው የማዳበሪያ ፋብሪካ በዩኒስኮ በተመዘገበው የያዩ የቡና የተፈጥሮ ሃብት Yayu Coffee Forest Biosphere reserve ላይ ችግር ይፈጥራል በሚል ተቃውሞ ሲቀርብበት ቆይቷል።
የማእድን ሚኒስቴርና የተፈጥሮ ሃብትና የደን ልማት ሚኒስቴር ፕሮጀክቱን በተመለከተ እውቅና ባይሰጡም ሜቴክ ስራውን በራሱ መጀመሩን ሰነዶች ያመለክታሉ።
የህንጻ ግንባታውን የሚያካሂደው ተክለብርሃን አምባየ የግንባታ ድርጅት ከሜቴክ ጋር በክፍያ ተጣልተው ስራውን ለ10 ወራት ያክል ካቋረጠ በሁዋላ፣ በቅርቡ እንደገና ስራውን ጀምሯል። ሜቴክ በበኩሉ እስካሁን በቂ ስራ ሳይሰራ የፕሮጀክቱን ከፍተኛ ገንዘብ ከወሰደ በሁዋላ፣ አሁን ተጨማሪ ገንዘብ መጠየቁ በሜቴክ የሚሰሩ ስራዎች አገሪቱን ለከፍተኛ ኪሳራ እየዳረጉዋት መሆኑን እንደሚያሳይ ዘጋቢያችን ገልጿል። ሜቴክ ስራዎችን በተሰጠው በጀት ፈጽሞ እንደማያውቅ በአመታዊ እቅዱ ላይ የቀረበው ዝርዝር ማስረጃ ያሳያል። ፕሮጀክቶች የሚጓተቱት በሙስና ምክንያት መሆኑን፣ ፕሮጀክቶቹ ከተጠናቀቁ በሁዋላም ቢሆን የጥራት ጉድለት ያለባቸው መሆኑን ሰነዶቹ ያመለክታሉ።
ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በቀድሞ የህወሃት ታጋዮች የሚመራው ሜቴክ ፣ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የአምበሳውን ድርሻ ይዟል።