ኢሳት (ግንቦት 8 ፥ 2009)
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት ከደንበኞቹ ያልተከፈለው የአገልግሎት ክፍያ ለፋይናንስ እጥረት እንደዳረገው ይፋ አደረገ።
አየር መንገዱ ለተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት መንግስታትና ተቋማት አገልግሎት የሰጠባቸው ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለረጅም ጊዜ ሳይከፈለው መቅረቱን ሲገለጽ እንደነበር ይታወሳል። ይኸው ለረጅም ጊዜ ሳይከፈል የቆየው ክፍያ በድርጅቱ የእለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖን ማሳደሩን የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም ኤየር ትራንስፖት ወርልድ ለተሰኘና በአቪየሽን ጉዳዮች ላይ ለሚያተኩረው መጽሄት አስረድተዋል።
አንጎላ፣ ናይጀሪያና፣ ሱዳን የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተለያዩ አገልግሎት ሲሰጥባቸው ከቆዩና ከፍተኛ የገንዘብ ክፍያ ካልፈጸሙት መካከል ዋነኞቹ መሆናቸውን ሃላፊው ለመጽሄቱ ገልጸዋል።
ሃገሪቱና የግል ተቋማቱ ለተጠቀሙት አገልግሎት ክፍያን በምን ምክንያት እንዳልፈጸሙ ግን አቶ ተወልደ የሰጡት ዝርዝር መረጃ የሌለ ሲሆን፣ አጠቃላይ የገንዘብ መጠኑም ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
ይሁንና በጉዳዩ ዙሪያ ከወራት በፊት ዘገባን አውጥተው የነበሩ የናይጀሪያ መገናኛ ብዙሃን የሃገሪቱ አየር መንገዶች በኢትዮጵያ አየር መንገድ ለተደረገላቸው የቴክኒክ አገልግሎት ክፍያን ሳይፈጽሙ መቆየታቸውን አመልክተዋል።
ይህንኑ ለረጅም ጊዜ ሳይከፈል የቆየውን ክፍያ ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በናይጀሪያ የሃገር ውስጥ በረራን በሚሰጠው የቻንቻንጊ አየር መንገድ ላይ ከጥቂት አመታት በፊት ክስ መስርቶ እንደነበርም ለመረዳት ተችሏል።
አንጎላና ሱዳንም አገልግሎትን ላገኙባቸው የተለያዩ ስምምነቶች ለአመታት ክፍያ ሳይፈጽሙ መቆየታቸው ታውቋል።
ሃገሪቱ ክፍያን ባለመፈጸማቸው ምክንያት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለፋይናንስ እጥረት ተጋልጦ እንደሚገኝ አቶ ተወልደ ለመጽሄቱ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቀጣዮቹ ጥቂት አመታት ውስጥ የሰራተኛ ቅነሳን ሳያደርግ በየአመቱ እስከ 20 በመቶ የሚሆን የወጪ ቅነሳን ለማድረግ እቅድ መያዙን ዋና ስራ አስፈጻሚው አክለው ገልጸዋል። አየር መንገዱ ከፍተኛ የፋይናንስ ችግር ውስጥ ነው ያሉት አቶ ተወልደ የግብር ክፍያ የአውሮፕላን ዋጋ እና የመሰረተ-ልማቶች ግንባታ ዋጋ መጨመር ፈታኝ ሆነው መቀጠላቸውንም አስረድተዋል።