ኢሳት (ግንቦት 8 ፥ 2009)
የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደህዴን) በትግራይ ክልል በ 12 ሚሊዮን ብር ያስገነባው ህንጻ መመረቁ ተዘገበ።
መንግስታዊው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኤዜአ) እንደዘገበው በአቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ የሚመራው የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ በትግራይ ክልል አዲገባሮ በተባለ ገጠር ቀበሌ የሰራው 12 ሚሊዮን ብር የወጣበት ትምህርት ቤት ሰኞ ዕለት ተመርቋል።
የደቡብ ክልል ለትግራይ ክልል ትምህርት ቤት ለመገንባት 12 ሚሊዮን ብር ያወጣው ደህዴን የተባለው ድርጅት ከ27 አመታት በፊት በዚህ ት/ቤቱ በተገነባበት ቦታ ስለተመሰረተ እንደሆነም ተመልክቷል።
ሆኖም ደህዴን ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ ከሁለት አመት በኋላ በ1985 የተመሰረተ እንደሆነ በይፋ እየተገለጸ የምስረታ በዓሉ በመከበር ላይ መሆኑ ይታወቃል።
የህወሃት ኢህአዴግ ቡድን ስልጣን ከያዘበት ከ1983 ጀምሮ የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት/ ኦህዴድ/ በሰሜን ሸዋ ደራ በ1982 መመስረቱ ሲገልጽ ቆይቶ፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ትግራይ ውስጥ ተመሰረተ የሚል መግለጫ በመስጠት ላይ መሆኑ ይታወሳል። ኦህዴድም በተመሳሳይ ት/ቤት ወይንም ሌላ ድረጅት በትግራይ ይገነባል ተብሎ ይጠበቃል።
የህወሃት መሪዎች ከቅርብ አመታት ወዲህ የሁሉ ነገር ማዕከል ትግራይና ህወሃት ነው የሚል አቋም በግልጽ በማራመድ ላይ ሲሆኑ፣ ወደዚህ የገፋቸው ምክንያት ግን በግልፅ አይታወቀም።